ቀጥታ፡

ሱዳናዊያን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በገንዘብ እንደሚደግፉ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2012 (ኢዜአ) ሱዳናዊያን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በገንዘብ እንደሚደግፉ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ በቅርቡ በተቀረጸው መርሃ ግብር ሱዳናዊያን የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።

ለህዳሴው ግድብ ግንባታ የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ በፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ይፋ ተደርጎ በተጀመረው መርሀ ግብር በአገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ ሱዳናዊያንም የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብሏል ሚኒስቴሩ።

በሱዳን ዋዲ ሃሊፋ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ አካሻ የሚባሉ ግለሰብና ሌሎች ሱዳናዊያን ኢትዮጵያ ከጎረቤትና ከአካባቢው አገራት ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ የአባይ ተፋሰስን ከግጭት መናኸሪያነት ይልቅ የዕድገት ማዕከል ለማድረግ እያከናወነች ያለውን ተግባር እንደሚደግፉም ገልጸዋል።

ሰዳናዊያኑ በቀጣይነትም የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ የአቅማቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑና ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆሙ አሳውቀዋል ሲል ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም