የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ ከኮሮና ቫይረስ ነጻ መሆናቸው ታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ ከኮሮና ቫይረስ ነጻ መሆናቸው ታወቀ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2012(ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ ከተያዘው ጃፓናዊ ጋር ንክኪ የነበራቸው ዶክተር ቶላ በሪሶ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተገለጸ።
ከ12 ቀናት በፊት ከጃፓናዊው ጋር ንኪኪ የነበራቸው ዶክተር ቶላን ጨምሮ 21 ሰዎች ነጻ መሆናቸውን በሐኪሞች እንደተገለጸላቸው ዶክተር ቶላ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በጃፓናዊው ላይ ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘ ከተገለጸበት ጊዜ አንስቶ ለብቻቸው ተቀምጠው የነበሩት ዶክተር ቶላ በተደረገላቸው ምርምራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል።
በቫይረሱ የተያዘው ጃፓናዊ ከእሳቸው በተጨማሪ በአርሲ ዞን ሁለት ትምህርት ቤቶችን ሲጎበኙ ንኪኪ አላቸው የተባሉት ሁሉም ሰዎች ነጻ መሆናቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ 5 ግለሰቦች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው 992 ሰዎች ባሉበት ቦታ ለ14 ቀናት የጤና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ አስታውቋል።