ቀጥታ፡

ምሁራን አገራዊ ሚናቸውን ሊወጡ የሚችሉበት መድረክ ሊመቻች ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ

አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 የኢትዮጵያ ምሁራን ለአገራዊ ጉዳዮች ሃሳብ የሚያመነጩበትና የሚከራከሩበት መስተጋብር በመፍጠር ለአመራር አቅም መጎልበት ሚናቸውን የሚወጡበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ። "ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትና አመራር" በሚል መሪ ሃሳብ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ያዘጋጀው 2ኛው አገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ዛሬ ተጀምሯል። በጉባኤው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀን ጨምሮ በርካታ የመንግስትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የስራ ኃላፊዎች፣ የምርምር ተቋም ተወካዮችና ምሁራን ተሳትፈዋል። የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አስተሳሰቦችንና የአመራር ብቃትን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎችም ቀርበው በጉባኤተኛው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። በዚሁ ጊዜ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ አሁን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከመቼውም ጊዜ በላይ ንቁ መሪ ይሻል። በመሆኑም የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ የሚያስቀጥል በቂ አመራር ለማፍራት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። የአመራር አቅም የሚጎለብተው ምሁራን በአገራዊ ሁኔታዎች ላይ የሚከራከሩበት መስተጋብር ሲፈጠር መሆኑንም አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል። የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚ ምሁራንን በማገናኘት በአገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብ አመንጭተው እንዲከራከሩ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። የአካዳሚው ፕሬዚዳንት አቶ አለምነው መኮንን በበኩላቸው ጉባኤው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አጀንዳዎችን ወደ ሰፊው መድረክ በማምጣት ምሁራን ለርእሰ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። አካዳሚው ብቁ አመራር ለማፍራት ይረዳው ዘንድ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በጥናትና ምርምር ለመደገፍ የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም አቶ አለምነህ አክለዋል። ጉባኤው ለአገር ልማት የሚበጁ ምሁራዊ ሀሳቦች፣ ጥቆማዎችና ልምዶች ይገኙበታል ተብሎ እንደሚታመንም  አቶ አለምነህ ገልጸዋል። በጉባኤው ጥናት ካቀረቡት ምሁራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጄሉ ኡመር በተለያዩ ተቋማት የሚስተዋሉ ድክመቶች መሰረታዊ ምክንያታቸው የአመራር አቅም አለመጎልበት መሆኑን ተናግረዋል። ይህንን ለመለወጥ መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ጠንካራ መሪዎችን ለመፍጠርና ያሉትን አመራሮች አቅም ለማጎልበት ደግሞ ዘርፉ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ተቋማት ሊስፋፉ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስትና የአመራር ጥበብ ላይ ሰፊ ክርክሮች ይደረጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም