ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ነብዩ ስሁልን በኃላፊነት ሾመ

መጋቢት 8/2012 ( ኢዜአ)  የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት

መምህር ነብዩ ስሁልን በኃላፊነት መሾሙን አስታወቀ፡፡

ኃላፊው የክልሉ ሕዝብ የአገራዊ ለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆን ተግተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አዲሱ ተሿሚ መምህር ነብዩ ስሁል ከብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ከአቶ አወሉ አብዲ ጋር በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

መምህር ነብዩ በአገሪቷ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሂደት በሕዝቡ ግፊትና ትግል የመጣ መሆኑን አስታውሰዋል።

"የመደመር ፍልስፍናም የኢትዮጵያ መገለጫ ሲሆን ለትግራይ ሕዝብ ደግሞ የመደመር ፍልስፍና ተቋም ሊባል ይችላል" ብለዋል።

ይህን እውነታ ታሳቢ በማድርግ በቀጣይ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝቡ ከአገራዊ ለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ዋነኛ የትኩረት ጉዳይ አድርጎ ይንቀሳቀሳል ነው ያሉት።

''ለውጡ ለትግራይ ሕዝብ ይገባዋል" ያሉት መምህር ነብዩ ሕዝቡ ለውጡን ይጠብቀዋል ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ፓርቲው በትግራይ ክልል ለማሸነፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ እውን ማድረግ ሌላው የጽህፈት ቤቱ ተግባር እንደሆነም አመልክተዋል።

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ እና በትግራይ ክልል ዞኖችና ወረዳዎች ጽህፈት እንደሚከፍት ጠቁመዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው "ፓርቲው ለትግራይ ሕዝብ ቃል በገባው መሰረት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል" ብለዋል።

ብልጽግና አገራዊ ፓርቲ መሆኑንና በሁሉም ክልሎች መንቀሳቀስ እንዳለበት ገልጸው እስካሁን ወደ ኋላ ለቀረው የትግራይ ክልል ጽህፈት ቤት ሰው መድቦ ሥራ ማስጀመሩን ጠቅሰዋል።

የፓርቲው ዋና ዓላማ እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓት እውን ማድረግ እንደሆነ አመልክተው "የትግራይ ሕዝብ ለዚህ ሲል ከፍተኛ ትግል ማካሄዱ ይታወቃል" ብለዋል።

በመሆኑም የክልሉ ሕዝብ አዲስ ከተመደቡት አመራሮች ጋር በመሆን ትክክለኛ ዴሞክራሲን እውን ለማድረግ እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም