ለውጭ ገበያ ከሚቀርብ የስጋ ምርት የአገሪቱ ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለውጭ ገበያ ከሚቀርብ የስጋ ምርት የአገሪቱ ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 ለውጭ ገበያ ከሚቀርብ የስጋ ምርት አገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሰራው ስራ ዝቅተኛ እንደሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ፡፡ የምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን የ2010 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም መነሻ በማድረግ የ2011 በጀት አመት መሪ እቅድን በዛሬው እለት ገምግሟል፡፡ በዚሁ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ መኩዬ እንደተናገሩት፤ አገሪቱ ወደ ውጪ ከሚላክ የእንስሳት የስጋ ምርት በተገቢው መልኩ ተጠቃሚ አልሆነችም። በተለይም የበሬ ስጋ ወደ ውጭ ለመላክ ከተያዘው እቅድ ማሳካት የተቻለው 23 በመቶ ብቻ መሆኑ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደሆነ የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህም ኢንስቲትዩቱ ወደ ውጪ የሚላክ የስጋ ምርት አቅርቦትን ለማሻሻል የሚያስችልና ወቅታዊ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ እቅድ ማዘጋጀት እንዳለበት አቶ ብርሃኑ አስገንዝበዋል። የእንሰሳትን ስጋ ወደ ውጪ የሚልኩ ፋብሪካዎች በራሳቸው እንስሳቱን በማደለብ በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡ የኢትዮጵያ የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀይለስላሴ ወረስ በበኩላቸው በአገሪቱ የእንስሳት ምርትን ወደ ውጪ የሚልኩ ቄራዎች ውስን መሆንና የአገር ውስጥ የስጋ ዋጋ ከውጭው የበለጠ መሆን የወጪ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የበሬ ስጋ ወደውጭ በመላክ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው ስምንት ሚሊዮን ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በአገሪቱ በቀን እስከ 3ሺህ እንስሳትን የሚያቀርብ ቄራ እየተገነባ በመሆኑ በቀጣይ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ የሚያድግበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ ቄራዎችም እንስሳቶችን በራሳቸው የማድለብና የማቅረብ ስራዎችን እየሰሩ በመሆናቸው በዘርፉ አበረታች ውጤት እንዲመጣ የሚያግዝ እንቅስቃሴ እንደሆነም አቶ ሀይለስላሴ ተናግረዋል፡፡ በተያያዘ የኢትዮጵያ የስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የመንግስትን የወጪ ቅነሳ መመሪያ ተከትሎ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ለመንግስት ተመላሽ ማድረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ለኢዜአ ገልጸዋል። የወጪ ቅነሳ መመሪያውን ተከትሎ መቀነስ ያለባቸውን ወጪዎች በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ውይይት መደረጉንና ለመንግስት ተመላሽ የሆነው በጀትም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም በስብሰባዎች ወቅት ለካኔተራና ኮፍያ፣ አጀንዳና ተያያዥ ህትመቶች፣ የምግብ መስተንግዶና የአዳራሽ ኪራይ የሚወጡ ወጪዎች እንዲቀሩ መደረጋቸው ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም በውጭ ሀገራት ለሚደረገው ጉዞ የሚወጣው ወጪ መቀነሱ ለተመላሽ በጀቱ ዋና ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።፡፡