ቀጥታ፡

ዋጋ በጨመሩ 130 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ደሴና ደብረ ብርሃን 07/07/2012  (ኢዜአ ) በደሴ ከተማና በሰሜን ሽዋ ዞን በበርበሬና በሌሎች የግብርና ምርቶች ላይ የተጋነነ ዋጋ በጨመሩ 130 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የየአካባቢው የንግድና ገበያ ልማት መምሪያዎች ገለፁ ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉ ረዳኢ ዛሬ እርምጃ ከተወሰደባቸው ነጋዴዎቸ ጋር በተደረገ ውይይት እንደገለጹት ሰሞኑን በተለያዩ ምርቶች ላይ አግባብ ያልሆነ የዋጋ ጭማሬ ተስተውሏል።

ችግሩን ለመፍታት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በተደረገ ጥናት ምርታቸውን በመጋዘን አስቀምጠው ያለምክንያት ዋጋ ጨምረው በተገኙ 30 የበርበሬና 23 የጤፍ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ድርጅቶቻቸውን የማሸግ እርምጃ ተወስዷል።

ነጋዴዎቹ ከ80 እስከ 85 ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ኪሎ ግራም በርበሬ እስከ 155 ብር ድረስ፤ አንድ ኩንታል ጤፍ ደግሞ ከ3 ሺህ 200 ብር ወደ 3 ሺህ 700 ብር ከፍ አድርገው ሲሸጡ በመገኘታቸው እርምጃው እንደተወሰደባቸው አስረድተዋል ።

የምርቶቹን  ዋጋ መጨመር ተከትሎም ሌሎች የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች ላይ ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ በመታየቱ ክትትልና እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የታሸጉት መደብሮች ሊከፈቱ የሚችሉት  በቀደመው ፍትሃዊ ዋጋ ለመሸጥ ሲስማሙ ብቻ ነው ብለዋል ።

ካልሆነ ግን የከተማ አስተዳደሩ ፍቃዳቸውን እስከ መሰረዝ የሚያደርስ እርምጃ ለመውሰድ  ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡

በደሴ ከተማ የአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ኮማንደር እንየው እንዳለው በበኩላቸው የፀጥታ ኃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ።

ከደላሎች ጋር ተመሳጥሮ የሚፈጠር የዋጋ ንረት የህብረተሰቡንና የአካባቢው ሰላም የሚነሳ ተግባር በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰቡ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ወደ ህጋዊ አሰራር መምጣት እንዳለበት አሳስበዋል ።

ከውይይቱ ተሳታፊ ነጋዴዎች መካከል አቶ አህመድ እሸቱ በሰጡት አስተያየት በየ15 ቀኑ ከ30 እስከ 40 ኩንታል በርበሬ ከደቡብና ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ዞኖች እያመጡ ደሴ ከተማ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡

እስከ አሁን አንድ ኪሎ በርበሬ ከ65 ብር በታች በማስመጣት ከ85 ብር በታች ይሸጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ሰሞኑን ግን የዋጋ ጭማሬ በመከሰቱ ጨምረው ለመሸጥ መገደዳቸውን ጠቅሰው መንግስትም የችግሩን ምንጭ በመረዳት የማስተካከል እርምጃ ከወሰደ እኛም የገበያውን ሚዛናዊነት ለመጠበቅ እንሰራለን ብለዋል ።

በተመሳሳይ በሰሜን ሽዋ ዞን የበርበሬ፣ የጤፍና የሌሎች የግብርና ምርቶች ዋጋ ድንገት በመጨመሩ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የማስተካከል ስራ እየወሰደ ነው ።

 በዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የስነ ልክ ባለሙያ አቶ ጥላሁን አበበ እንደገለፁት ባለፉት 15 ቀናት በተደረገው ክትትል 70 የበርበሬና 7 የጤፍና ሌሎች ነጋዴዎች መደብር ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።

ነጋዴዎቹ በኪሎ 120 ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ኪሎ ግራም በርበሬ 180 ብር ፣ 3 ሺህ 300 ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ኩንታል ጤፍ ደግሞ 400 ብር በመጨመር 3 ሺህ 700 ብር ሲሸጡ የተገኙ ናቸው ።

አግባብ ያልሆነ ዋጋ በመጨመር የህብረተሰቡን የኑሮ ውድነት በሚያናጉ ነጋዴዎች ላይም የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ባለሙያው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም