የጤና ቢሮው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው አለ

110

ድሬዳዋ ፣ መጋቢት 7/2012 (ኢዜአ)  በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ስንታየሁ ደበሳ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት ድሬዳዋ ከተጎራባች ጅቡቲና ሶማሌላንድ ጋር በቅርብ ርቀት ትገኛለች።

በዚህም በባቡር ጣቢያ እና በድሬዳዋ አለም አቀፍ አውሮፕላን  ማረፊያ ውስጥ የጤና ባለሙያዎች ቡድን ተደራጅቶ የምርመራ ሥራ እየተካሄደ ነው፡፡

ከተጎራባች ሶማሌ ክልል ጋርም  በመቀናጀት በድሬዳዋ -ደወሌ-ጅቡቲ የክፍያ መንገድ ተጓዦች የሚደረገው ምርመራ የማጠናከር ሥራም እንዲሁ፡፡

በተጓዳኝም በቫይረሱ የሚጠረጠሩ ሰዎችን ለይቶ ማቆያ በ"ነምበር ዋን" ጤና ጣቢያ መዘጋጀቱን ያመለከቱት ኃላፊዋ፤  ቫይረሱ የሚገኝባቸውን ሰዎች ደግሞ ተገቢው ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ስፍራ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡

የማከሚያ ቦታ ጥበት ካጋጠመም በሣቢያን ጠቅላላ ሆስፒታልና በድሬዳዋ ምድር ባቡር ሆስፒታል ህክምና እንደሚሰጥም አመልክተዋል፡፡

ከሆስፒታሎቹ ለተውጣጡ የጤና ባለሙያዎች ተገቢውን ስልጠና መሰጠቱንና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን በቂ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች እየተሟላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

እንደ ወይዘሮ ስንታየሁ ገለፃ  ህብረተሰቡ በመገናኛ ብዙሃን እየተላለፈ የሚገኘውን የጥንቃቄ መልዕክት መከታተል የሁጊዜ ተግባሩ ማድረግ አለበት፡፡

በድሬዳዋ  እስካሁንም በኮሮና ቫይረስ የተያዘም ሆነ የተጠረጠረ ሰው አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም