ቀጥታ፡

''የአቧራ ማእበል'' በጤንነት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት

መቀሌ፣መጋቢት 07/12 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ሰሞኑን የተከሰተውና ''የአቧራ ማእበል'' በመባል የሚታወቀው የአቧራ ብናኝ በጤንነት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ የዘርፉ ምሁራን አሳሰቡ።

በክልሉና በተወሰኑ አጎራባች ክልሎች የታየውን የአቧራ ብናኝ ተከትሎ በህብረተሰቡ ላይ የጤና ችግር እንዳያስከትል ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን አሳስበዋል ።

የአቧራ ብናኙ የአካባቢ ሙቀት ሲጨምርና አሸዋማ አፈር በበዛባቸው አካባቢዎች በቀላሉ በነፋስ ሃይል እየተነሳ በአየር ላይ የሚጓዝ ክስተት መሆኑን የገለፁት በመቐለ ዩኒቨርስቲ የፊዚክስና የስነህዋ ትምህርት ክፍል አስተማሪ ዶክተር ሃይለስላሴ ገብረማሪያም ናቸው ።

‘’የአቧራ ማእበሉ’’ ሃይለኛ የፀሃይ ሙቀት ወደ መሬት ሲያርፍ በሚፈጠር የአየር ግፊት ምክንያት የሚከሰት መሆኑን ተናግረዋል።

ክስተቱ በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኘው አሸዋ በቀላሉ ከመሬት እንዲነሳ በማድረግና በነፋስ ሃይል ከግብፅና ከሱዳን ተነስቶ  ወደ ሀገራችን እንዲገባ ማድረጉን አስረድተዋል ።

በዚሁ የትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ገብረ ጊዎርጊስ አብርሃ በበኩላቸው ክስተቱ ሞቃታማ የአየር ሁኔታ ሲከሰት የሚፈጠር  እንጂ ከአየር መዛባት ጋር ፍጹም ግኑኝነት የለውም ብለዋል።

ከአቧራው ጋር በተያያዘ ሁኔታ በጤንነቱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርበት መክረዋል ።

አሁን በትግራይና አጎራባች ክልሎች የተከሰተው የአቧራ ብናኝ ባለፉት ዓመታት ይከሰት ከነበረው ተመሳሳይ ክስተት ጋር ሲነፃፀር በስፋትና በቆይታ ጊዜው የጨመረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የትግራይ ቅርንጫፍ የአየር ትንበያና ትንተና ባለሙያ አቶ ጎይቶኦም ቀለም ናቸው።

ባለፉት አመታት በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ለአጫጭር ሰዓታት የሚቆይ ተመሳሳይ ክስተት ያጋጥም እንደነበረም ባለሙያው አመልክተዋል።

የአሁኑ የአቧራ ብናኝ ግን ከመጋቢት 2 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ በሰቲት ሑመራ አካባቢ መከሰቱንና ስርጭቱን ቀስ በቀስ እየሰፋና የቆይታ ጊዜውም የተራዘመ መሆኑን ተናግረዋል።

የአቧራ ብናኙ በሌላ ነፋስ ተገፍቶ እስኪሄድ ድረስ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም ነው አቶ ጎይቶኦም ያሳሰቡት ።

 በገጠር አካባቢም የአቧራ ብናኙ ወደሚጠጣ ውሃ በቀላሉ ሊገባ ስለሚችል ህብረተሰቡ የጉድጓድ ውሃን በቀጥታ ከመጠጣት ይልቅ አፍልቶና አጣርቶ ሊጠቀም እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሪአ ኢሳያስ ናቸው።

የአቧራ ብናኙ በህብረተሰቡ ጤና ላይ እያስከተለ ስላለው ችግር ዝርዝር ጥናት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተለይ የመተንፈሻ አካላትን በጨርቅ መሸፈን እንደ አንድ የጥንቃቄ አማራጭ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል ።

የሰቲት ሁመራ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትርሃስ አዲስ የአቧራ ብናኙ የአስም በሽታቸውን በመቀስቀስ እያስቸገራቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በተለያዩ የመተንፈሻ አካላቸው ላይ የጤና እክል እየፈጠረባቸው መሆኑን ያመለከቱት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ፈለገ ገብረመስቀል ናቸው።

የአቧራ ብናኙ ባስከተለው የአየር መታፈን ትናንት የኢትዮጰያ አየር መንገድ ወደ መቀሌ እና ላሊበላ ሊያደርጋቸው የነበሩት በረራዎች እንዲሰረዙ ማድረጉን መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም