በተሸከርካሪ አደጋ የእናትና ልጅ ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
በተሸከርካሪ አደጋ የእናትና ልጅ ህይወት አለፈ
ደሴ መጋቢት 7/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ከደሴ ወደ ኮምቦልቻ ከተማ በመጓዝ ላይ የነበረ ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ዛሬ ባደረሰው አደጋ የእናትና ልጅ ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።
በዞን ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ነፃነት አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ልጅ አዲስ ባለ ሦስት እግር ባጃጅ ገዝቶ ከእናቱ ጋር እያሽከረከረ ሲጓዝ ረፋዱ ላይ በመገልበጡ ነው።
መነሻው ደሴ ሆኖ ኮምቦልቻ ከተማ ቀበሌ ሁለት "ሃረጓ" ተብሎ በሚጠራው ገደል ገብቶ በመገልበጡ የእናትና ልጅ ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።
የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ቢሆንም መንገዱ ገደላማ፣ ጠመዝማዛና አስቸጋሪ በመሆኑ በፍጥነት ሲያሽከረክር አደጋው እንደደረሰ መገመቱንም አመልክተዋል፡፡
ነዋሪነታቸው ከምቦልቻ ከተማ የነበረው የሟቾቹ አስክሬን ለምርመራ ወደ ደሴ ሪፈራል ሆስፒታል መላኩንና ቤተሰቦች እንዲረከቡ የሚደረግ መሆኑን ኮማንደሩ አስረድተዋል።