በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰራ ተቋም አለመኖር መብታቸውን ለማስከበር እንቅፋት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰራ ተቋም አለመኖር መብታቸውን ለማስከበር እንቅፋት ፈጥሯል

አዲስ አበባ፣መጋቢት 7/2012 (ኢዜአ) የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ብቻ የሚመለከቱ ተቋማት አለመኖር መብታቸውን በአግባቡ የማስከበር ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተገለጸ።
አካል ጉዳተኞች የሚገጥሟቸው ችግሮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ ተቋም ሊኖር እንደሚገባም ተመልክቷል።
የአካል ጉዳተኞች መብት አማካሪና የህግ ባለሙያ አቶ ይልቃል አሳቤ እንዳሉት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት መፈረሟና የሲቪል ማህበረሰብ ህጉ መሻሻል ለመብታቸው መከበር አዎንታዊ አስተዋፅኦ አለው።
የመንግስት ፍቃደኝነትና እየተከተለ ያለው የመደመር ፍልስፍናም እንዲሁ የራሱ ጠቀሜታ አለው ይላሉ።
ያም ሆኖ አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ ሁሉን አቀፍ የህግ ማዕቀፍ አለመኖሩን የገለጹት ባለሙያው፣ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የወጡ የተለያዩ ህጎች አፈጻጸምም ክፍተት እንደሚታይበት ጠቁመዋል።
የሥራ ስምሪት አዋጁ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ቢገልጽም በተግባር አፈጻጸሙን የሚከታተል ኃላፊነት ያለው አካል አለመኖሩን በመጥቀስ።
አካል ጉዳተኞች ቅሬታና አቤቱታ ሲኖራቸውም መደበኛ ሂደትን ተከትለው እያገኙት ያሉት መፍትሄ አጥጋቢ እንዳልሆነ አቶ ይልቃል ጠቅሰዋል።
በመደበኛው አሰራር በተቋማት ስለ አካል ጉዳተኞች በሚገባ ግንዛቤው ኖሮት የሚሰራ የሰው ኃይል እጥረት መኖሩንም ነው ያመለከቱት።
በሌሎች የዓለም አገራት የአካልጉዳተኞችን ጉዳይ ብቻ የሚመለከቱ ተቋማት መኖራቸውን ገልፀው በኢትዮጵያ መሰል አሰራር አለመኖር የአካል ጉዳተኞችን መብት የማስከበር ሥራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው አስረድተዋል።
"ችግሩን በመፍታት አካል ጉዳተኞችን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ አካል ጉዳተኞች ላይ አተኩሮ የሚሰራ መሰል ተቋም ያስፈልጋል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ ለመብት ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የኀብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
በኮሚሽኑ የሴቶች፣ ህጻናትና አካልጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ትሁን ሽፈራው እንዳሉት ኮሚሽኑ የመንግስት ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ በመሆን በኩል ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ጥናት አካሂዷል።
የጥናቱን ግኝት ለሁሉም የመንግስት ተቋማት እንደሚሰጥ ገልፀው፣ ተቋማቱ የማስተካከያ ሥራ ስለመስራታቸው በኮሚሽኑ በኩል ክትትሉ እንደሚጠናከር አስረድተዋል።
በቀጣይ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሰራ ዘርፍ እንዲኖር እየተሻሻለ ባለው የኮሚሽኑ መቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ መካተቱንም ጠቁመዋል።
ይህም የአካል ጉዳተኞች መብት በተሻለ መጠን እንዲረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ወይዘሮ ትሁት አስረድተዋል።