በሐረሪ 43 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለአገልግሎት ተዘጋጁ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ 43 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለአገልግሎት ተዘጋጁ
ሐረር ሰኔ 22/2010 በሐረሪ ክልል 43 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የሚያመነጩ የአራት ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ ተጠናቀው ለአገልግሎት መዘጋጀታቸውን የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ገለጸ፡፡ የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አብዶሽ እንደገፈለጹት የውሃ ጉድጓዶቹ ቁፋሮ የተካሄደው ከሐረር ከተማ 76 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው በድሬዳዋ አስተዳደር አሶሊሶ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡ ከውሃ ጉድጓዶቹ መካከል ሶስቱ ከሐረሪ ክልል ባለፈ ለአዴሌ፣ ሐረማያና አወዳይ ከተሞች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ቀሪው ደግሞ ቁፋሮው በተካሄደበት ድሬዳዋ አስተዳደር አሶሊሶና ሁላ ሁልል ገጠር ቀበሌዎች የሚኖሩ 600 አባራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ከእንዚህ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የሚመነጨው ውሃ ቀደም ሲል ከድሬዳዋ አሶሊሶ ገጠር ቀበሌ እስከ ሐረሪ ከተዘረጋው የውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧ ጋር በመግጠምና በከፍተኛ የኤሌትሪክ ኃይል አማካኝነት ተስቦ እንዲያገለግል የተመቻቸ ነው፡፡ የውሃ ማከፋፈያና ሌሎችም ተጓዳኝ መገልገያዎች እንዳሉት ያመለከቱት ስራ አስኪያጁ ለስራው ማስፈጸሚያ ወጪው የተሸፈነው በክልሉ መንግስት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተቋማቱ ግንባታ በክልሉና በአካባቢው ያሉ ከተሞች የሚታየውን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ያቃልላል ተብሏል። በባለስልጣኑ የአሶሊሶ ውሃ ፕሮጀክት አተባባሪ አቶ መሀመድ አብዲ በበኩላቸው በአምስት ወራት ውስጥ የተጠናቀቀው የውሃ ጉድጓዶቹ ቁፋሮ ከድሬዳዋ እስከ ሐረር ከተማ ድረስ የሚገኙ ነዋሪዎችን የንጹህ ውሃ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በድሬዳዋ አስተዳደር አሶሊሶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሻፊ አብዱላሂ በሰጡት አስተያየት ለመንግስት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት በአቅራቢያቸው የንጽህ መጠጥ ውሃ ተመቻችቶላቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የነበረባቸው ችግር መቃለሉን ጠቅሰው ወደ አካባቢያቸው ከመጠጥነት አልፎ የመስኖ ልማት ለማካሄድ እንደሚያስችላቸውም አመልክተዋል፡፡ "በበጋ ወራት የውሃ እጥረት የሚታይበትና አካባቢያችን ደግሞ ዳገታማ በመሆኑ የውሃ አቅርቦቱ ይቀንሳል"ያሉት ደግሞ በተለምዶ ጎርጊስ በሚባለው አካባቢ የሚኖሩት አቶ ደጉ አበበ ናቸው። አዲስ የተቆፈረው የውሃ ጉድጓድ ይህን ችግር በማቃለል ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡