የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተቋማት እንዲዘጉ ተወሰነ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተቋማት እንዲዘጉ ተወሰነ
መጋቢት 7/2012 የኢትዮጵያ መንግስት በኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ትምህርት ተቋማት እንዲዘጉና ሁነቶች እንዲታገዱ ወሰነ፡፡
በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) በኢትዮጵያ እስካሁን አምስት ሰዎች መያዛቸው ሲረጋገጥ ሦስቱ ጃፓናዊያን፣ ሁለቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ታውቋል።
አምስተኛው ቫይረሱ የተገኘበት ኢትዮጵያዊ ደግሞ በዱባይ ነዋሪ እንደነበረ ተመልክቷል።
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በተገኙበት ውይይት አካሂዶ ውሳኔዎችንም አሳልፏል።
ውሳኔው የተላለፈው በጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በኩል የውሳኔው ምክር ሀሳብ ከቀረበና የኮሚቴው አባላት ከተወያዩበት በኋላ ነው።
በዚህም መሰረት በመላ አገሪቷ ትላላቅ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ስፖርታዊ ውድድሮች እንዳይካሄዱ ተወስኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት ከቫይረሱ ጋር ተያይዞ ሕብረተሰቡ አላስፍላጊ ፍርሃትና ሽሽት ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል።
በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች 80 በመቶዎቹ ምንም ህክምና ሳያገኙ፤ 15 በመቶ ደግሞ በህክምና እንደሚድኑ እንዲሁም 5 በመቶዎቹ የጽኑ ሕሙማን ህክምና እንደሚደረግላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በኢትዮጵያም ቫይረሱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ትላልቅ የመንግስትም ሆኑ የግል ስብሰባዎች፣ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ሳምንት እንዲዘጉ ተወስኗል።
ስፖርታዊ ክንውኖችና ሕዝባዊ ስብሰባዎችም ለቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት እንዳይካሄዱ ተከልክሏል።
አነስተኛና አስፈላጊ የሆኑ ስብሳባዎች በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ክትትል በሚያደርግበት ሁኔታ እንዲደረጉ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ባሉበት ሆነው በሽታውን እንዲከላከሉ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
"የኮሮና ቫይረስ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ዜጎች ለጉዳት እንዳይጋለጡ በእምነት ተቋማትም ባይሰበሰቡ ይመረጣል" ተብሏል።
ሕብረተሰቡ ከመንግስት ውሳኔ ጎን ለጎን የንጽህና ዘመቻ እንዲያካሄድ ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እሳቸውና ሚኒስትሮቹ በእጅ የመታጠብ ዘመቻውን ጀምረዋል።
በዘመቻው ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስትም አልኮል፣ ሳሙናና የፊት መሸፈኛ ማስክ ያቀርባል ብለዋል።
ይህን ተከትሎ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግስት አስጠንቅቋል።
የመንግስት ተሽከርካሪዎች ጠዋት እስከ 1፡30 መደበኛ ስራቸውን ካከናወኑ በኋላ ከሁለት ሰዓት ጀምሮ በትራንስፖርት የህዝብ መጨናነቅን ለመቀነስ ህብረተሰቡን ያገልግሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
መምህራንም ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ በበጎ ፈቃደኝነት ለማገዝ እንዲረባረቡ ተጠይቋል።
በርከት ያለ ተሽከርካሪ ያላቸው የግል ተቋማትም ህብረተሱቡን እንዲተባበሩ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መገናኛ ብዙሃንም ትክክለኛውን መረጃ ለህዝብ ማድርስ አለባቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳሉት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የጤና ሁኔታ አሁን ላይ የተሻለ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል።