ኢትዮጵያ የዱባይ ኤክስፖን እምቅ ሀብቷን ለማስተዋወቅ ትጠቀምበታለች

113

አዲስ አበባ፣መጋቢት 7/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በዱባይ ኤክስፖ 2020 የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም እምቅ ሀብቷን ለማስተዋወቅ በዝግጅት ላይ መሆኗን የኤክስፖው ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዱባይ ኤክስፖ ኢትዮጵያ ራሷን የምታስተዋውቅበት ሥፍራ /ፓቪሊዮን/ ግንባታ ተጠናቋል።

“አዕምሮዎችን በማስተሳሰር ወደፊትን መፍጠር!” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ከጥቅምት እስከ መጋቢት 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኤክስፖው የኢትዮጵያ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሃይማኖት ጥበቡ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ ዝግጅቱን ራሷን ለዓለም የምታስተዋውቅበት መድረክ ታደርገዋለች።

ለዚህም ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በዋነኝነት የኤክስፖ ሥራውን ያስተባብራሉ።

በኤክስፖው ለሚከናወኑ ተግባራት 65 ሚሊዮን ብር መመደቡንም ወይዘሮ ሃይማኖት አስታውቀዋል።

የአገሪቷን የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያሳዩ መድረኮች እንደሚዘጋጁም አክለዋል።

ከኤክስፖው በኋላ ዘላቂ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር የሚፈጥሩ ተግባራት ይከናወናሉም ብለዋል።

ከቱሪዝም አኳያ ሉሲን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች እንደሚተዋወቁም ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ግንባታ በዱባይ አስተዳደር የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እየተከናወነ ሲሆን፣የግንባታው ውጫዊ ሥራ መጠናቀቁን ኃላፊዋ አስታውቀዋል።

ግንባታውን እስከ ነሐሴ 2012 ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በኤክስፖው የምታሳያቸውን ምርቶች፣ አገልግሎቶችና ትርኢቶች 750 ሺህ ሰዎች እንደሚጎበኙት ይጠበቃል።

በኤክስፖው 550 የቢዝነስ ለቢዝነስ ትስስሮችና 250 ጊዜ የሚዲያ ሽፋን ለማግኘትም ታቅዷል።

በኤክስፖው የካቲት 23 ቀን 2013 ዓ.ም "የኢትዮጵያ ቀን" የሚከበር ሲሆን፣ በዕለቱ ባህላዊና ታሪካዊ ትርዒቶች ይቀርቡበታል።

በኤክስፖው 192 አገራት በተሳታፊነት፣ 25 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በጎብኚነት ይጠበቃሉ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሻንጋይ ቻይናና በሚላን ኢጣሊያ በተካሄዱ ኤክስፖዎች ተሳትፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም