ቀጥታ፡

ቀይ መስቀል ለ300 ሺህ ነፍሰ ጡር እናቶች ነፃ የአንቡላንስ አገልግሎት ሰጠ

ጎንደር (ኢዜአ) መጋቢት 7/2012  የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ብሄራዊ ማህበር በመላ ሀገሪቱ ለ300 ሺህ ነፍሰ ጡር እናቶች የአንቡላንስ አገልግሎት መስጠቱን ገለፀ ፡፡

የብሄራዊ ማህበሩ ዋና ጸሃፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ ለኢዜአ እንደገለፁት ማህበሩ ባለፉት ስድስት ወራት ነፃ የአንቡላንስ አገልግሎቱን የሰጠው በ9 ክልሎችና የሁለት ከተማ መስተዳድሮች ባቋቋማቸው 320 የአንቡላንስ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች አማካኝነት ነው፡፡

አገልግሎቱ በመጓጓዣ እጦት ወደ ህክምና ተቋማት ሳይደርሱ በወሊድ ምክንያት በቤታቸው ውስጥ ህይወታቸውን የሚያጡ ነፍሰ ጡር እናቶችን ለመታደግ ያለመ መሆኑን አስረድተዋል ።

ብሄራዊ ማህበሩ በሚሰጠው የ24 ሰአት የአንቡላንስ አገልግሎት በየቀኑ ከ530 በላይ አንቡላንሶች እያሰማራ እንደሚገኝም ዋና ጸሃፊው ተናግረዋል፡፡ 

ማህበሩ በዘንድሮው ዓመት ከ700 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች የአንቡላንስ አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ በመጀመሪያው መንፈቀ ዓመት ከ300 ሺህ በላይ እናቶች ተጠቃሚ አድርጓል ።

ባለፈው አመትም በበጎ ፈቃደኛ አባላቱ አማካኝነት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ እናቶች የአንቡላንስ አገልግሎት መሰጠቱን ዶክተር መሸሻ ተናግረዋል ።

የማህበሩ አንቡላንሶች ደጃፋችን ድረስ መጥተው ወላዶችን ወደ ህክምና ጣቢያ በማድረስ የነፍሰ ጡር እናቶችን እንግልት አቃልለውልናል ያሉት በማእከላዊ ጎንደር ዞን የጭልጋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አታላ ሞላልኝ ናቸው፡፡

ቀደም ባሉት ጊዚያት ምጥ የተያዘች ሴት ሶስት ሰአት በሚፈጅ የእግር ጉዞ በሰው ሸክም አይከል ጤና ጣቢያ ትደርስ ነበር ያሉት ወይዘሮ አታላ የማህበሩ አንቡላንስ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወዲህ ግን በ30 ደቂቃ ለህክምና መድረስ እንደተቻለ ገልፀዋል ።

በወረዳው የገለድባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እናንዬ ዋሴ በበኩላቸው አንቡላንስ ወደ አካባቢያችን ከመጣ ወዲህ ቤት ውስጥ የምትወልድ ሴትም ሆነ በህክምና እጦት ህይወቷ የሚያልፍ ነፍሰጡር የለችም ብለዋል ።  

በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ 34 ዞኖችና 132 ወረዳዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን የከፈተው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ብሄራዊ ማህበር ከ6 ሚሊዮን በላይ መደበኛ አባላት እንዳሉት ከዋና ጸሃፊው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም