ቀጥታ፡

ለግጭት ምክንያት የነበረው ቦታ ለቤተክርስቲያን ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

መጋቢት 7/2012  በአዲስ አበባ 22 አካባቢ ከቤተክርስትያን ግንባታ ጋር የተነሳው ውዝግብ ምላሽ በማግኘቱ  የግንባታው መሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

የቤተ ክርስቲያኑን ግንባታ  የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ  ናቸው፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ የየሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳሳት፣ ምዕመናንና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ኃይለ አባ ወልደ ገብርኤል ነጋሽእንደተናገሩት፤የአዲስ አባበ ከተማ አስተዳደር በሀዘናቸውና በደስታቸው ጊዜ ከጎን በመቆም ለችግሩ ፈጣን  ምላሽ በመስጠቱ ምስጋና አቅርበዋል።

ሰላም ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት የሁሉም እምነት ተከታዮች ችግሩን ለመፍታት ላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ችግሮች ሲፈጠሩ በመደጋገፍ የመፍታት ባህሉ  ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩሉ ከዚህ በፊት የተፈጠረው ችግር ዳግም እንዳይከሰት ቤተክርስቲያን በትኩረት መስራት እንዳለባት አሳስቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በመወከል በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ቤተክርስቲያኗ ልጆቿን በስነ ምግባር ታንፀው አገር ወዳድ እንዲሆኑ የምታደርግ በመሆኗ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

ችግሩ ሊደርስ የቻለው የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ችግሮች በተያዘበት ወቅት መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ችግር የደረሰው በመንግስት በኩል ለሃይማኖት ቦታ ለመስጠት የተዘጋጀ ደንብና መመሪያ ባለመዘጋጀቱ እንደሆነም ገልፀዋል።

ሌሎች ካርታ የሌላቸው የእምነት ቦታዎች ስላሉ የሃይማኖቱ ተከታዮች በማስተዋልና በማገናዘብ ከመንግስት ጋር በመወያየት ያለውን ችግር መፍታት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 22 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 'ህገ-ወጥ' ግንባታ በሚል ጥር 27 ቀን 2012 ዓ.ም ሌሊት ላይ በተፈጠረ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉ ታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም