በኢትዮጵያ ሶስት ተጨማሪ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሶስት ተጨማሪ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተያዙ
መጋቢት 6/2012 በኢትዮጵያ ሶስት ተጨማሪ ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡
መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም በኮሮናቫይረስ መያዙ ከተረጋገጠው ግለሰብ በተጨማሪ ሶስት ሰዎች ተይዘዋለል።
ሚኒስቴሩ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ከተገኘ በኋላ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከግለሰቡ ጋር ንክኪ የነበራቸው ሰዎችን ሲከታተል ቆይቷል።
ኢንስቲትዩቱ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመተባበር 117 ሰዎችን ለይቶ ክትትል እያደረገና ናሙና እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጿል።
ክትትል ከተደረገላቸውና ናሙናቸው ከተወሰደው መካከል ሶስቱ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል።
በበሽታው የተያዙት የ44 እና የ47 ዓመት ጃፓናውያን እንዲሁም የ42 ዓመት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም መግለጫው ጠቁሟል።
በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዙ የተረጋገጠበት ጃፓናዊ በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝና ክትትል እየተደረገለት እንደሆነ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።
የበሸታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የኢትዮጵያ መንግስት በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች በመከታተል አፋጣኝ ርምጃ በመውሰድ እየሰራ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ ከሌሎች አገሮች ጋር በትብብር እየተሰራ ስለመሆኑም ገልጿል።