የህዳሴ ግድባችንን ከዳር ማድረስ ይጠበቅብናል--- ዶክተር አባተ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድባችንን ከዳር ማድረስ ይጠበቅብናል--- ዶክተር አባተ
ደሴ፣ መጋቢት 06/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን አጠናክረን የህዳሴ ግድባችንን ከዳር ማድረስ ይጠበቅብናል ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው "ግድቡ የኔ ነው" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ከህዝብ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
ዶክተር አባተ በውይይቱ ወቅት " የአባይ ግድብ የሁሉም አሻራ ያረፈበት አንጡራ ሃብታችን በመሆኑ ከተጋረጠብን ድህነት ሊያላቅቀን የሚችል የተስፋ ስንቃችን ነው" ብለዋል፡፡
ሆኖም ግድቡ እንዲስተጓጎል በግብጽ ቀስቃሽነት የሚደረገው ዘመቻ ተቀበይነት የሌለውና የኢትዮጰያዊያን ጠንካራ አንድነትና ህብረት የሚጠይቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
"መንግስት ለግድቡ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት ወቅት የፖለቲካችን ጡዘት የህብረተሰቡን አንድነት መሸርሸር የለበትም፤ ውስጣዊ አንድነታችንን አጠናክረን ግድቡን እውን ማድረግ ይጠበቅብናል "ብለዋል፡፡
ከ55 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በጨለማ እየኖረ በተፈጥሮ ሀብቱ ከመጠቀም የሚገታው እንደሌለ ያመለቱት ዶክተር አባተ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው፤ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ጭምር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
"ግብፅ መገናኛ ብዙሃኗ እና ምሁሮቿን ተጠቅማ ለምታደርገው የጥፋት ቅስቀሳ ኢትዮጵያ በሰከነ መንገድ መልስ መስጠት አለባት " ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትብብር ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ በዛብህ ናቸው።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራንን ግንዛቤ በመፍጠርና ህብረተሰቡን ለልማት በመቀስቀስ ግድቡ እንዲፋጠን ከማድረግም ባለፈ በተለያዩ ቋንቋዎች ለዓለም ማስተዋወቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ኤርሚያስ መኮንን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ተካፍለን እንብላ ባለች አደራዳሪ የተባሉ ጫና ለመፍጠር መሞከራቸው ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል፡፡
አሁንም ግድቡ እስኪጠናቀቅ የዞኑን ህዝብ በማስተባበር የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ገልጸው እስካሁን 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ድጋፍ መደረጉንም አመልክተዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ከበደ ወልደሩፋየል በሰጡት አስተያየት ለግድቡ ከ100 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውንና ግድቡ እስከሚጠናቀቅም እገዛቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ስራ ኃላፊዎችና መምህራን፣ የደቡብ ወሎና የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ነዋሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡