መጪው ምርጫ በሠላም እንዲካሄድ ወጣቶች በስክነት መጓዝ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መጪው ምርጫ በሠላም እንዲካሄድ ወጣቶች በስክነት መጓዝ አለባቸው
መጋቢት 6/2012 መጪው ምርጫ በሠላም እንዲካሄድ ወጣቶች በስክነትና በጥበብ በመጓዝ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አስገነዘበ።
ፓርቲው አገር አቀፍ የወጣቶች ጉባኤ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በጉባኤው ላይ ወጣቶች ለአገር ሠላምና አንድነት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፏል።
ከዚህ ባለፈም ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣቶች በወቅታዊ የሠላም ሁኔታ ላይ ፓርቲው መወጣት በሚገባው ኃላፊነት ዙሪያ ጥያቄ አቅርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል።
የኢዜማ የወጣቶች ጉዳይ ተጠሪ ወጣት ዘላለም አሰፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአገሪቷ በአሁኑ ወቅት ፖለቲካውን ተከትሎ የመጡ ዜጎችን ማፈናቀልና አንተ ከዚህ ጎሳ አይደልም አይነት አስተሳሰቦች ወጣቱ ተባባሪ ባለመሆን የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
በኢትዮጵያ ሠላም እንዲረጋገጥ የፖለቲከኞችና ማህበረሰብ አንቂዎች ያላቸው ድርሻ ጉልህ መሆኑን ተገንዝበው ሠላምና አንድነትን ማጠናከር ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብሏል።
ወጣቶች ለሠላም መረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንዳቸው የተናገረው ወጣት ዘላለም፤ ''በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ልቦናችን ከፍተን በማስተዋል መንቀሳቀስ አለብን'' ሲል አመልክቷል።
እንደ ወጣት ዘላለም ገለጻ፤ አሁን አገሪቷ ሙሉ በሙሉ መረጋጋት ባልቻለችበት ሁኔታ ምርጫ እየመጣ መሆኑ ወደፊት ትልቅ የቤት ስራ መኖሩን እንሚያመላክት ገልጿል።
''በመሆኑን ወጣቱ ምርጫውን በሰላማዊ ሁኔታ፣ በትዕግስት፣ በማስተዋል ቃኝቶ ፍትሃዊ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል'' ነው ያለው።
የፓርቲው ሊቀ መንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ''ወጣቶች ምርጫው በሠላም እንዲያልፍ ታሪክ መስራት ይጠበቅባቸዋል'' ብለዋል።
''ሰውን ማክበር አገርን ማክበር ነው'' ያሉት አቶ የሺዋስ፤ ወጣቱ አገሪቷን የማክበር ትልቅ ኃላፊነት እንደተጣለበት አስገንዝበዋል።
ወጣቶች የአገርን ክብር የሚነካ ማንኛውንም ግለሰብም ይሁን የፖለቲካ ድርጅት እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኅብረተሰቡ ውስጥ ለተለያዩ ጥቅሞች ብለው ልዩነትን የሚያሰፉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ያለፈውን ታሪክ እያነሱ ቂምና ጥላቻ እንዲያብብ የሚሰሩ መኖራቸው ያነሱት ተሳታፊዎቹ፤ ድርጊቱ አገርን አደጋ ውስጥ ሳይከት መታረም እንደሚኖርበት አመልክተዋል።