ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ብሔራዊ ማህበር ከ335ሺህ ለሚበልጡ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ አደረገ

ጎንደር፣ መጋቢት 06/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ብሔራዊ ማህበር በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ችግር ለተጋለጡ ከ335ሺ ለሚበልጡ ወገኖች የሰብአዊ አገልግሎት ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

ብሄራዊ ማህበሩ በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በግጭት ሳቢያ ቤታቸው ለተቃጠለባቸው አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ያስገነባቸውን 120 መኖሪያ ቤቶች ትላንት አስጎበኘቷል፡፡

የማህበሩ ዋና ፀሐፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭት ንብረታቸው ለወደመባቸውና ለተፈናቀሉ ወገኖች የእለት እርዳታ ፈጥኖ በማቅረብ ሰብአዊ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከ335ሺ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ችግር ለገጠማቸው ወገኖች ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በአማራና ደቡብ ክልሎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖችም ከ117 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

በዘላቂ ልማት በኩልም ከ700ሺ በላይ የሚሆኑ ወገኖች የንጹህ መጠጥ ውሃን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ዶክተር መሸሻ  አስታውቀዋል።

ብሄራዊ ማህበሩ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባቋቋማቸው መድኃኒት ቤቶች አማካኝነትም ከ3 ሚሊዮን 500ሺህ ለሚበልጡ  ወገኖች በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረጉንም አብራርተዋል፡፡

በብሄራዊ ማህበሩ የሰሜን ጎንደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታለል ታረቀኝ ማህበሩ በግጭቱ ምክንያት ቤታቸው ለተቃጠለባቸው 120 ለሚሆኑ ወገኖች ቤቶቹን መገንባቱን ገልጸዋል።

ቤቶቹ የተገነባላቸው በእድሜ የገፉ፤ አቅመ ደካሞችና አካል ጉደተኛ  አባወራና እማወራዎች ናቸው።

ማህበሩ በሁለቱ ዞኖች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ገንብቶ ላጠናቀቃቸው ቤቶች ከ4 ሚሊዮን 400ሺህ ብር በላይ  ወጪ ማድረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር የጭልጋ ወረዳ ነዋሪ  ወይዘሮ እናንዬ ዋሴ በሰጡት አስተያየት አምና በአካባቢ ተከስቶ በነበረው  ግጭት ቤታቸው እንደተቃጠለባቸው አስታውሰዋል።

"ቀይ መስቀል ገንብቶ በሰጠን መኖሪያ ቤት ዳግም ወደ መኖሪያ ቀዬ በመመለሴ ደስታየ ወሰን የለውም" ብለዋል፡፡እማሆይ ፈንታ መልኬ በበኩላቸው የ80 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ እንደሆኑ አመልክተው"ቀይ መሰቀል በሰራልኝ ቤት እንደ ልቤ ተኝቼ ለመነሳት በቅቻለሁ" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በግጭቱም መጦሪያቸው የነበሩ አራት በጎችና አንድ የእርሻ በሬ እንዲሁም መኖሪያ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸውም አውስተዋል።

በቤቶቹ ጉብኝት ወቅት ዋና ፀሐፊውን ጨምሮ የብሄራዊ ማህበሩ ቦርድ አባላትና በግጭቱ ሳቢያ ቤታቸው የተቃጠለባቸው ሰዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም