በኮምቦልቻ ኮሮናን ለመከላከል ከውጭ የሚመጡ ሰዎችን በማቆያ ቦታ የማጥራት ስራ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኮምቦልቻ ኮሮናን ለመከላከል ከውጭ የሚመጡ ሰዎችን በማቆያ ቦታ የማጥራት ስራ እየተካሄደ ነው
ደሴ፣ መጋቢት 6/2012 (ኢዜአ) በኮምቦልቻ ከተማ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከውጭ ሀገር የሚመጡ ሰዎችን ማቆያ ቦታ በማዘጋጀት የማጣራት ስራ እየተካሄደ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ የሚስተዋለውን ፈጣን የኢንቨስትመንት እድገት ተከትሎ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ፋብሪካዎች በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች ይኖራሉ፡፡
ምርታቸውንም ቀጥታ ወደ ውጭ ወስደው የተለያዩ ግብዓቶችን ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡና ሌሎችንም በማቆያ ቦታ የማጣራት ስራ እየተካሄደ ነው።
ይሄው ስራ ከተጀመረ ከ15 ቀናት በፊት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ለዚህም በኮሮና ቫይረስ መያዝና አለመያዛቸውን የሚያረጋግጥ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በቂ ስልጠና በወሰዱ በስምንት የጤና ባለሙያዎች እየተመራ መሆኑን ኃላፊው አመላክተዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኩን ጨምሮ 12 የስጋት ቦታዎች ተለይተው እያንዳንዳቸው ከውጭ የሚመጡ ሰዎችን ለ14 ቀናት ማቆያ ቦታ በማዘጋጀትም የመለየት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
እስካሁንም 15 ሰዎችን በመለየት በማቆያ ቦታ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ከእነዚሁ ውስጥም አምስቱ አስራ አራት ቀን ሞልቷቸው ጤነኛ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
"ቫይረሱ ወደ ከተማው እንዳይገባ ከፌደራልና ክልል መንግስት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው "ያሉት ኃላፊው በተደረገው ክትትል አንድ የውጭ ዜጋ ናሙናው አዲስ አበባ ተልኮ ነጻ መሆኑ ተረጋግጦ መለቀቁንም ጠቁመዋል፡፡
ከትላንት ጀምሮ ደግሞ በኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያ የተሳፋሪዎችን ሙቀት በመለካት ልዩ ክትትል መጀመሩንም ጠቅሰው ፤ በከተማው ክትትል ማድረጊያና ማቆያ ቦታ እየተመቻቸ መሆኑንም አብራርተዋል።
የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ሰይድ በበኩላቸው የፓርኩ ዘጠኙም ሸዶች
( ቤቶች) በአራት የውጭ ባለሃብቶች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡
ቫይረሱን ለመከላከል ለሁሉም ባለሃብቶች ግንዛቤ ተፈጥሮ ወደ ውጭ ሂደው ሲመጡ ለ14 ቀን የሚቆዩበትና ክትትል የሚደረጉበት ማዕከል ማዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በማቆያ ቦታ ክትትል ከሚያደርግባቸው 15 የውጭ ዜጎች መካከልም አስሩ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሰራተኞች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አሁንም ስልጠና ከወሰዱ የጤና ባለሙያዎች ጋር ተቀናጅተው በትኩረት እየሰሩ መሆኑንና የፓርኩ የዕለት ተዕለት ተግባር በአግባቡ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ በሽታን ለመከላከል የስጋት ቦታዎችን በመለየት ቅድመ-ዝግጅት መደረጉን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ቀደም ሲል ገልጾ ነበር።
በተመረጡ አካባቢዎች ቫይረሱን መመርመር የሚያስችሉ ቁሳቁሶች መቅረባቸውን በተለይም ተጓዥ የሚበዛባቸው ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላና ኮምቦልቻ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራም ኢንስቲትዩቱ በወቅቱ አስታውቀዋል።
"የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመቀናጀት ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን መረጃ ስለሚሰጥ ህዝቡ ሳይደናገጥ በሚሰጡ መግለጫዎች መሰረት መመራት ይኖርበታልም " ብለዋል።