የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ወደ መቐለና ላልይበላ የሚያደርገውን በረራ ሰረዘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ወደ መቐለና ላልይበላ የሚያደርገውን በረራ ሰረዘ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 6/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ መጋቢት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ መቐለና ላልይበላ የሚያደርገውን በረራ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት መሰረዙን አስታወቀ።
አየር መንገዱ ዛሬ ጠዋት ወደ ጎንደር፣ አክሱምና ሽሬ ይደረጉ የነበሩ በረራዎች መስተጓጎላቸውን ጠቁሟል።
በአንዳንድ የአገር ውስጥ መዳረሻዎች ባጋጠመ አስቸጋሪ የአየር ጠባይ ምክንያት የተስተጓጎሉ በረራዎች የአየር ሁኔታው ሲሻሻል የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል።
አየር መንገዱ ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የአየር ጠባይ ምቹነት መረጃ ሲደርሰው በረራውን እንደሚያስቀጥል አስታውቆ፤ ይህ የአየር ሁኔታ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ሊቀጥል እንደሚችል ከኤጀንሲው መረጃ ማግኘቱን ገልጿል።
በረራው ሲቀጥል አየር መንገዱ በጥሪ ማዕከሉ በኩል ለደንበኞቹ ጥሪ እንደሚያስተላልፍ ገልጾ፤ ለተፈጠረው መጉላላት ይቅርታ መጠየቁን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።