የጤና ባለሙያዎች በአገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ባለሙያዎች በአገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል
መጋቢት 5/2012(ኢዜአ) የጤና ባለሙያዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን በማስጠበቅ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ አሳሰቡ።
ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲና የአዳማ ጀነራ ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ 49 የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ከ 1 ሺህ 700 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቀዋል።
በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ምረቃ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደተናገሩት ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት በመጠቀም ማህበረሰቡን በአግባቡ ማገልገል ይኖርባቸዋል።
በተለይም የህክምና ተመራቂዎች ሩህሩህ፣ ተገልጋይን አክባሪና ተንከባካቢ በመሆን ከወላጆቻቸውና ከህብረተሰቡ ለተደረገላቸው አስተዋጽኦ ተገቢ አገልግሎት በመስጠት መካስ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
ሃገሪቷ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥታ የምታከናውናቸውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና የኮሮና ቫይረስ ስጋትን የመከላከል ስራ በስኬት ለመወጣት የተማረ የሰው ኃይል እገዛ ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።
በህክምና ዶክተሬት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ዶክተር ሚካኤል ስንታየሁ እንደተናገረው፤ ወቅቱ ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ የሚያስፈልግበት በመሆኑ ባገኘው እውቀትና ክህሎት ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ ነው።
በየጊዜው የሚያጋጥሙ የጤና ስጋቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት ለመከላከልም ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን በትጋት ለመስራት የሚያስችል አቅም ከዩኒቨርሲቲው እንዳገኘም ጠቁሟል።
የዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች 1ሺህ 233 ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥም 34ቱ የህክምና ዶክተሮች ናቸው።
በተመሰሳይ ዜና የአዳማ ጀነራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ 15 የክምና ዶክተሮችን ጨምሮ 500 የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎችን ባስመረቀበት ወቅት የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደተናገሩት የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማሳደግ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ወሳኝ ነው።
በጤና ፕሮግራም የተነደፉትን ስትራተጂዎች ለማሳካትና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከመንግስት የጤና ተቋማት በተጓዳኝ በዘርፉ የተሰማሩ የግሉ ሴክተሮች እገዛም ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኮሌጁ ዲን አቶ ዲሪባ ደገፋ በበኩላቸው ኮሌጁን የጤና ዘርፍ የጥናትና ምርምር የልህቀት ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ገልጸው 15 የህክምና ዶክተሮችን ጨምሮ ዛሬ የተመረቁት 500 የህክምና ባለሙያዎች የዚሁ ጥረት ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምሩቃኑም በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የሚፈልገውን የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ከማሳደግ አኳያ የገቡትን ቃል ጠብቀው በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።