የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በስምንት ወራት የ26 ቢሊየን ብር ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በስምንት ወራት የ26 ቢሊየን ብር ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ
አዲስ አበባ መጋቢት 5/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከሐምሌ 2011 እስከ የካቲት 2012 ዓ.ም ድረስ የ26 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ።
ይህም ከእቅዱ በግብይት ዋጋ 11 በመቶ፣ በመጠን ደግሞ አንድ በመቶ ብልጫ ያሳየ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የግብይት ዋጋው ወደ 24 ከፍ ብሏል፡፡
በእነዚህ ወራት ውስጥ የቡና፣ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተር፣ የማሾ፣ የነጭና የቀይ ቦሎቄ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ አገበያይቷል።
ከምርቶቹ ውስጥ ቡና 38 በመቶ፣ ሰሊጥ 35 በመቶ፣ እና አኩሪ አተር 12 በመቶ በግብይት መጠናቸው እንደ ቅደም ተከተላቸው ተቀምጠዋል፡፡
ምርት ገበያው በየካቲት ወር 4 ነጥብ 42 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ያገበያየ ሲሆን፣ ለእነዚህም 97 ሺህ 382 ቶን ምርቶችን አቅርቧል፡፡
በግብይቱም በየካቲት ወር የሰሊጥ ምርት በ1 ነጥብ 52 ቢሊዮን ብር የተገበያየ ሆኖ በወሩ ከተገበያዩ ምርቶች ቀዳሚውን ቦታ ይዟል፡፡
ከዚህ ውስጥ የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ 78 በመቶ ድርሻ በመውሰድም ቀዳሚውን ደረጃ አስመዝግቧል፡፡
ምርት ገበያው 25 ሺህ 354 ቶን ሁሉንም የቡና አይነቶች በማቅረብ 2 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን ምርት ገበያው የላከው መረጃ ያመለክታል።