ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የወሰዷቸው አዎንታዊ እርምጃዎች ወቅታዊ የፖለቲካ ውጥረትን ያረግባል - የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ

አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፉት ጥቂት ወራት የወሰዷቸው "አዎንታዊ እርምጃዎች ወቅታዊውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ጉልህ ሚና አለው" ሲል የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ገለጸ። ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ህዝብ ተስፋ ያደረገውና የፈጠረው አጋጣሚ እንዳይባክን ከመንግስት ብዙ የሚጠበቅ ቢሆንም "ሌሎች አካላትም የበኩላቸውን ገንቢ ሚና ሊጫወቱ ይገባል" በማለትም ገልጿል። ጉባኤው ዛሬ "ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር ህዝብ ተስፋ የጣለብ አጋጣሚ እንዳይባክን" በሚል መሪ ሃሳብ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል። በሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አመሀ መኮንን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ጥቂት ወራት የወሰዷቸው አዎንታዊ እርምጃዎች ወቅታዊውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ ጉልህ ሚና አለው። ጉባኤው ከዚህ ቀደም በእነዚህ ፈታኝ ወቅቶች በአገሪቷ በሁሉም አካባቢዎች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ሲመረምር፣ ሲመዘግብና ጥሰቶቹ እንዲቆሙ ሲጠይቅ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን የተወሰዱያሉ እርምጃዎች አዎንታዊ መሆናቸውን አመላክቷል። በእስር ላይ የቆዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም አክቲቪስቶች ክሳቸው ተቋርጦ በይቅርታ እንዲፈቱ መደረጉን ያስታወሱት አቶ አመሀ፤ በአገር ወስጥና በውጪ አገር ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ማድረጋቸው ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል በየደረጃው ያለ ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ማበርከት እንደሚገባው ተናግረዋል። መንግስትም የዜጎች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትንም ሆነ የሃሳብ ልዩነቶችን እንዲከበርና እንዲስተናገድ ማድረግ እንዳለበት ጠቁሟል። የህግ አስከባሪ አካላትና ተቋማት ገለልተኛ፣ ለህግ ተገዥና የዜጎችን መብት ጠባቂ ሆነው እንዲያገለግሉ እንደገና እንዲደራጁ ማድረግ እንደሚገባም ተጠቁሟል። በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ሰብዓዊ፣ ህጋዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችና ችግሮች ዘለቄታዊ መፍትሄ በመስጠት ረገድም እንዲሁ። የተለያዩ የሲቪክ ማህበራትም አሁን በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ከምን ጊዜውም በበለጠ የህዝቡን የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ጥያቄ በማሰማት ረገድ ገንቢ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በሌላ በኩል የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ፣ በአገሪቷ በሁሉም አካባቢዎች ተዘዋውረው የመኖርና የመስራት መብታቸው ከተከበረ ዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ የበኩላቸውን "ማድረግ ይጠበቅባቸዋል"። በአጠቃላይ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የተጀመሩ የለውጥ አንቅስቃሴዎችን በብቃትና በሃላፊነት ስሜት የድርሻውን አንዲወጣ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤው ጥሪውን አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም