ምሁራን ስለ ህዳሴ ግድብ በጥናት የተደገፈ መረጃ ለዓለም ማህበረሰብ እንዲያሳውቁ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን ስለ ህዳሴ ግድብ በጥናት የተደገፈ መረጃ ለዓለም ማህበረሰብ እንዲያሳውቁ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2012 (ኢዜአ) ምሁራን ስለ ህዳሴ ግድብ በጥናትና ምርምር የተደገፈ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በስፋት የማሳወቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ምሁራን ተከታታይ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ መረጃ የመስጠት ልምዳቸው አነስተኛ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገልጸዋል።
የአባይ ወንዝ ለኢትዮጵያ የልማት ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት እንዲሰጠውና አገሪቷ ወንዙን ተጠቅማ ልማቷን እንድታፋጥን የሚጠበቀውን ያህል ድጋፍ አለመደረጉንም አንስተዋል።
በአባይ ወንዝ ላይ ግብፆች የበላይነት ማሳየት የሚሞክሩት የአገራቸው ምሁራን ለዓለም አቀፉ ማህበረተሰብ በሚሰጡት መረጃና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ በመሠራታቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ምሁራን ጥናትና ምርምር ላይ ያተኮሩ ትክክለኛ መረጃዎችን ለአለም ማህበረሰብ በማድረስ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በሰጡት አስተያየት ''ምሁራን የሚሰጡት አስተያየት ከስሜት ባልወጣ ሀቅን ፣ እውቀትን እና የምርምር ውጤትን መሰረት ያደረገ ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን የመጠቀም መብቷን ማሳየት፤ ኢትዮጵያ ምንም አይነት አማራጭ የሃይል ምንጭ የሌላት መሆኑን እንዲሁም ያላት የወንዝ ምንጮችን የመጠቀም መብቷን በደንብ ለዓለም ማሳየት መቻል አለባት፤ ይህ ደግሞ ከምርምር መመንጨት አለበት።''
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህግ አማካሪ አምባሳደር ኢብራኢም እድሪስ በበኩላቸው ፤ ''በግብጽ ውስጥ እኮ ብዙ ጊዜ በመደጋገም የምናገረው በሳምንት ሁለት ሶስት መጽሃፍት ይጻፋል፤ አብዛኞቹ ፕሮፌሰሮች ናቸው። የሚጽፉት ዩኒቨርስቲ ውስጥ ግን መንግሥት ይደግፋቸዋል"ብለዋል።
"እነዚህ ሰዎች እንዲጡ እንዲያድጉ መደገፍ መቻል አለብን። እነዚህ ሰዎች ናቸው ከሶስተኛ ወገን ከምሁራን በሪሰርች ተደግፎ የሚሰጥ ትምህርት ነው ዋጋ ያለው በዓለምአቀፍ ደረጃ ላይ ተቀባይነት ያለው፤ ስለዚህ ማገዝ መቻል አለብን።'' በማለት ገልጸዋል።
ምሁራኑ በአባይ ወንዝና በህዳሴ ግድብ ላይ በየተቋማቸው የተደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በቂ አለመሆናቸውንም በማንሳት፤ አሁን በህዳሴ ግድቡ ላይ ያለውን አገራዊ መነቃቃት የበለጠ ለማሳደግና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ ለመሥራት የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጁ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ እንዳሉት''በተለይ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ተቋማት ይህን አጀንዳ አለምአቀፍ አጀንዳ የማድረግ የሰብዓዊ መብት ጭምር ስለሆነ አሁን የተጠቃሚነት የኢኮኖሚ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያ እናቶች መብት ይገባቸዋል።"
ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ''እውቀት ላይ የተመረኮዘ ፣በምርምር ላይ መሰረት ያደረገ ዲፕሎማሲ የውሃ አጠቃቀም ፣የውሃ ጥናት ኢነርጂ አጠቃቀም ላይ በጣም መሥራት አለብን። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባለችው ገንዘብ በህዳሴ ግድብ ላይ በአባይ ውሃ ላይ በርካታ ምርምሮችን ይሠራል። ግን አሁን ያለው ኢንቨስትመንት በቂ ነው ብዬ አላስብም፤ እነዚህ ጥናቶች ተጠናክረው ህብረተሰቡ ላይ ወርደው የአገሪቷን ችግር መፍታት ሲችሉ ነው ዲፕሎማሲውም ሊጠናከር የሚችለው በእውቀት ሲመሠረት ነው።'' በመለት ነው የገለጹት።
በአባይ ወንዝ ላይ ከተፈረሙ ስምምነቶች ውስጥ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ያገኘው እንደ አውሮፓዊያኑ በ2015 በኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መሪዎች የተፈረመው ''የመርህ ስምምነት'' ብቻ ነው።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1929 በታላቋ ብሪታኒያና በግብጽ መካከል የተፈረመው ስምምነት የላይኞቹ ተፋሰስ አገሮች የአባይን ውሃ ለመጠቀም የግብጽን ይሁታ እንዲያገኙ ያስገድዳል።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1959 ግብጽና ሱዳንም ኢትዮጵያን በማግለል የአባይን ውሃ ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ስምምነት ፈርመዋል።
እነዚህ ስምምነቶች በኢትዮጵያ በኩል ምንም አይነት ተቀባይነት የሌላቸው ቢሆኑም ግብጽ ግን ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ግፊት ማድረጓን ቀጥላለች ነው ያሉት።
ሆኖም በአባይ ወንዝ ላይ የኢትዮጵያን ፍትሃዊ የመጠቀም መብት በማሳወቅና በግብፅ በኩል ያለውን የተዛባውን የጥቅም ፍላጎት ምሁራኑ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማስረዳት ይኖርባቸዋል ተብሏል።