ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የመጣው ተፅዕኖ ይበልጥ እንድንሠራ አነሳስቶናል- የግድቡ ግንባታ ሰራተኞች

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2012 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክትል ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው፤ ግድቡ በቀጣዩ ክረምት የውኃ ሙሌት ለመጀመር በሚያችለው ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሠራተኞች እንደተናገሩት፤ በግድቡ ግንባታ ላይ ያለው የሥራ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜትና መነሳሳት እየተካሄደ ነው።

"ከግድቡ ጋር ተያይዞ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከውጭ ሃይሎች የሚነሱና የምንሰማቸው ማናቸውም ተፅዕኖዎች እልህና ብርታት እንጂ የፈጠሩብን መዳከም የለም" ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በአንድነትና በጋራ በመቆም ለግድቡ ግንባታ ስኬት ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ የጠየቁት ሠራተኞቹ ግንባታውን ያለ ምንም ድካም እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

አስተያየቱን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጠው መልካም አገኘሁ "በፊት ስሥራው ከነበረውና አሁን ደግሞ እንደዚህ አይነት ተጽኖዎች ሲመጡ ጠዋት ተነስቼ እንድሠራ ነው ያደረገኝ እንጂ እንድሰንፍ ወይም ወደኋላ እንድል ሳይሆን ይበልጥ እንድሠራ አድርጎኛል፤ ይህ በግድቡ ላይ የመጣው ተጽኖ አይደለም ባለኝ ጉልበትና ከሚከፈለኝ ክፍያም አውጥቼ ብሰጥ ደስተኛ ነኝ በዚህ ሰአት" ብሏል።

 እንግዳው ደረስ በበኩሉ፤ "እኛ ከዚህ ላይ ስላለን ብቻ ሳይሆን በያገሩ ያሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚከፍሉት መሰዋትነት ነው።ማንም ሰው በየሃገሩ ሆኖ ለዚህ ግድብ ብዙ መሰዋት ስለሚያደርግ እኛ እጃችን እዚህ ይሁን እንጂ ማንም ሰው ከዚያ ሆኖ በተዘዋዋሪ ግድቡን እየገደበው ነው ።ስለዚህ ይሄ ግድብ ተገድቦ ለሁሉም ዜጋ ደርሶ ደስታውን እንዲያገኝ ነው እኔ የምፈልገው" ይላል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ በላቸው ካሳ እንዳሉት፤ የግድቡ ግንባታ ከምንጊዜውም በላይ እየተፋጠነ ይገኛል።

ግንባታው ለአዳዲስ ኮንትራክተሮች ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም የሥራ ተቋራጮች በመናበብ እየሠሩ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የግድቡ ግንባታ ሂደት በቀጣዩ ወርሃ ክረምት ውኃ ለመሙላት በሚያስችለው ፍጥነትና ጥራት እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አፈፃፀምም 71 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም