ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 5/2012 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድርስ የህዝቡ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለግንባታው እውን መሆን ህዝቡ ከፍተኛ ተሳትፎና ድጋፍ እያደረገም ይገኛል።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በገንዘብ፣ በጉልበት እና በእውቀት ጭምር በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች ድጋፍ እያደረጉ የቆዩ ሲሆን አሁንም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የ8100 A አጭር የፅሁፍ መልእክት፣ የቦንድ ሳምንት እንዲሁም የደረት ፒን በማዘጋጀት ለሽያጭ ማቅረብ አሁን ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች መካከል ይጠቀሳሉ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፅህፈት ቤት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሪሶርስና ፕሮጀክት ማኔጅመንት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ሰለሞን ተካ ለኢዜአ እንደገለጹት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ይከናወናል።
በመርሀ-ግብሩ መሰረትም ከመጋቢት 15 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ይከናወናል።
“አሻራዬን አኑሬያለሁ” የሚል ፅሑፍ የታተመበትና የህዳሴ ግድብ ምስል ያረፈበት የደረት ፒን ሽያጭ ለማከናወንም ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ “እስካሁን ድረስ የተተገበሩ የህዳሴ ግድቡ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብሮች ውጤታማ ነበሩ”።
በ2007 እና በ2008 ዓ.ም በሁለት ዙሮች በተካሄደ የ8100A የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ-ግብር በመጀመሪያው ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በሁለተኛው ዙር 49 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውሰዋል።
ግድቡ የህዝቦችን አንድነትና መተባበርን የሚያንጸባርቅ የጋራ ግድብ በመሆኑ ህዝቡ ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በሦስተኛው ዙር የ8100A የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ከሳምንት በፊት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።
የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሩ ለስድሰት ወር የሚቆይ ሲሆን በዚህም 20 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።
በተመሳሳይ ከመጋቢት 15 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት 70 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታሰቡ ተገልጿል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከኅብረተሰቡ 13 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አፈፃፀምም 71 በመቶ መድረሱ ይታወቃል።