የኮሮናን ቫይረስን ለመከላከል የአኗኗር ዘይቤን መቀየር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናን ቫይረስን ለመከላከል የአኗኗር ዘይቤን መቀየር ይገባል
አዲስ አበባ መጋቢት 4/2012(ኢዜአ) የኮሮናን ቫይረስን ለመከላከል ህብረተሰቡ የአኗኗር ዘይቤውን መቀየር እንዳለበት የጤና ሚኒስተሯ ዶከተር ሊያ ታደሠ አሳሰቡ፡፡
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ጃፓናዊ መገኘትን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ቀደም ሲል የተጀመረው የጥንቃቄ ስራ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በመግለጫውም የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት በሽታው ባለበት እንዲቆም የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የቫይረሱ ምልክቶችም ከጉሮሮ ጋር የተያያዘ ህመም፣ ሳል እና ትኩሳት መሆኑን የገለጡት ሚኒስትሯ ምልክቶቹን ያሳየ ሰው በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይኖረበታል ብለዋል፡፡
ቫይረሱ በተለይም ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተያያዘ ህመም ያለባቸው ሰዎች ላይ እንደሚጸና ገልጸው ዕድሜያቸው ከፍ ያሉትን የማጥቃት ባህሪ እንዳለው አሳውቀዋል፡፡
ተጨማሪ ሌሎች ህመሞች ባሉባቸው ሰዎች ላይ ህመሙ የከፋ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ቫይረሱ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተክትሎ ለመከላከል መስራት እንጂ መደናገጥና አጉል ፍራቻ ከበሽታው እኩል አደገኛ በመሆኑ ይህ ሊወገድ ይገባል ብለዋል፡፡
የኮሮናን ቫይረስን ለመከላከል ህብረተሰቡ በተለይ የእጅ ንጽህናውን መጠበቅ እና ከቅርብ ንክኪም ራሱን ሊቆጥብ ይገባል ሲሉ መክረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ በኮሮና ቫይረስ መጠቃት ማለት መሞት ማለት አለመሆኑን ገልጸው በዚህ ቫይረስ የሚያዝ አብዛኛው ሰው፣ ቀላል ህመም ከያዘው በኋላ ይድናል ብለዋል።
ህብረተሰቡም ከዚህ ቀደም ከለመደው የአኗኗር ዘይቤ ማለትም ከመጨባበጥ፣ እጅን ካለሳሙና መታጠብ እና አይንና አፍንጫን ከመነካካት መቆጠብ እንዳለበት አሳሰበዋል፡፡
መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር በሽታው በቻይና ከተገኘበት ወቅት ጀምሮ ቫይረሱ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባና ከገባም ጉዳቱን ለመቀነስ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ሰባት ሚኒስትሮች ያሉበት የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ግብረ-ሃይል የተቋቋመ ሲሆን፥ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉት የቴክኒክ ግብረ ሃይልም ተቋቁሟል።
በአሁኑ ወቅት በሽታው በ134 አገራት መከሰቱ ታውቋል፤ በተለያዩ አገራት ወደ ማቆያ ክፍሎች የገቡ ተጠቂዎች በአብዛኛው ከህመሙ ድነው መውጣታቸውም ታውቋል፡፡