አባይና የአባይ ልጆች የልብ ትርታ - ኢዜአ አማርኛ
አባይና የአባይ ልጆች የልብ ትርታ
አባይና የአባይ ልጆች የልብ ትርታ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 4/2012(ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በባህል፣አኗኗር፣ብሄር፣ ሃይማኖትና ሌሎች መገለጫዎች ልዩነት ይዘው ሲታዩ እንደ ቅርንጫፍ የተለያዩ የሚመስሉ በተግባር ሲታዩ ደግሞ አንድ የአገራዊ ስሜትና የአብሮነት ባህል ግንድ ላይ የቆሙ መሆናቸውን በርካቶች ይመሰክራሉ።
ከነዚሁ ህዝቦች ቀዬ የሚመነጨውና ልክ እንደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ጥቁር የሚያደላ ጠይም ቀለም ያለው የበረሃው ሲሳይ 'አባይ ወንዝ' ደግሞ ይህችን አገርና ህዝቦቿን በዓለም እንዲታወቁ ካደረጋቸው የተፈጥሮ ገፀ-በረከት አንዱ ነው።
አባይ ወንዝና ኢትዮጵያውያን በአንድ አገር ተወልደው ለዘመናት በአንድ አገር መኖራቸው ደግሞ አንዳቸው ለአንዳቸው የማይጨካከኑ የአንድ እናት ልጆች አድርጓቸዋል።
ኢዜአ ሪፖርተር በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ ከተማ ፣በወሎ ደሴ ከተማና በትግራይ ኮረም አካባቢ ያናገራቸው ዜጎችም በተለያየ አካባቢ፣ በተለያየ ባህልና ሃይማኖት፣በተለያየ ብሄርና ማንነት ስለ አባይ አንድ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው መሆኑን በአንደበታቸው ይመሰክራሉ።
ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የኢኮኖሚ ጥያቄ ብቻም ሳይሆን የአንድነትና የአብሮነታቸው ምንጭ መሆኑንም ይገልፃሉ።
የህዳሴው ግድብ በሚገጥሙት ችግሮች ውስጥ አብረው እንደሚያልፉና ለግድቡ ስኬት የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚያደርጉም እንዲሁ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት ያለበት የግንባታ ሁኔታ 71 ነጥብ 6 በመቶ የደረሰ ሲሆን በቀጣዩ የክረምት ወቅት በሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት እንዲጀምር ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ ነው።