የኢትዮጵያ የውስጥ አለመረጋጋት ለግብጽ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ምሁራን አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የውስጥ አለመረጋጋት ለግብጽ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ምሁራን አስታወቁ
አዲስ አበባ መጋቢት 4/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተፈጠረው የውስጥ አለመረጋጋት ግብጽ በአባይ ግድብ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ እንድትሰራ ዕድል መፍጠሩን ምሁራን ገለጹ።
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በአባይ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ከሁሉም የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ሶስት የውይይት የመነሻ ሀሳቦች በተለያዩ ምሁራንና በግድቡ የድርድር ሂደት ቀጥተኛ ተሳትፎ በነበራቸው አካላት ቀርቧል።
የመጀመሪያው የውይይት መነሻ "በአባይ ላይ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት'' ሲሆን የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴና አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደፕሮፌሰር ባህሩ ገለጻ “ግብጽ በአባይ ውሃ የመጠቀም ፍላጎት ያሳየችው ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲሆን የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀምና በተለይ ኢትዮጵያ ከውሃው ያላትን ታሪካዊና ህጋዊ መብት እውቅና እንዳታገኝ በማድረግ ነው” ብለዋል።
የግብጽ መንግስታት በአባይ ውሃ ላይ መርህን ያልተከተለ አካሄድ ሲከተሉ እንደነበር ጠቅሰው መንግስታቱ ሃይልን የመጠቀም ሙከራቸው ጭምር ሊከሽፍ መቻሉን ነው ያስታወሱት።
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1975 እስከ 1976 ግብጽ በምጽዋ በኩል ጦር አዝምታ ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ እንደቀረ ነው ፕሮፌሰር ባህሩ የተናገሩት።
አገሪቱ ውሃውን በፍትሃዊና ምክንያታዊነት ከመጠቀም ይልቅ እኔ ብቻ የሚለው መርኋ በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል።
ግብጽ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የአባይን ውሃ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም የሚያስችላትን ሙከራ የማድረግ ልምድ እንዳላት አንስተው በተለይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመፍጠር ስለግድቡ የተሳሳተ መረጃ እንደምትሰጥ ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድርን ሲከታተሉ የነበሩት አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ፣ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው እንዲሁም ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ከድርድር ሂደቱ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ በዝርዝር አቅርበዋል።
በዚህን ጊዜ ግብጽ በአባይ ውሃ ላይ ያቀረበችው የድርድር ሀሳብ በኢትዮጵያ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ነው ተደራዳሪዎቹ የተናገሩት።
በመድረኩ በአባይ ላይ የተደረጉት ስምምነቶች አሁን ላይ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም ግድቡን በህብረተሰብ ፍላጎት እንዴት መገንባት ይቻላል? በሚል ምክክር ተደርጓል።