ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ግድቦች ጥቅማቸው የጎላ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ ዝግጁ ነን...ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ግድቦች ጥቅማቸው የጎላ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ ዝግጁ ነን...ምሁራን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4/2012(ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ኢትዮጵያ የምትገነባቸው ግድቦች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው የጎላ እንዲሆን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ምሁራን ገለጹ።
ከአገር ውስጥና በውጭ ያሉ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን ዛሬ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በአባይ ላይ ያደረጉትን ውይይት ባለስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቀዋል።
በውይይቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ምሁራንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለማት ያሉ የኢትዮጵያ ምሁራን በቴክኖለጂ በመታገዝ ተሳትፈዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ምሁራኑ ስምንት ነጥብ የያዘ የአቋም መግለጫ በማውጣት ግድቡ በተባለው ጊዜ ተጠናቆ የታለመለትን ዓላማ እንዲመታ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር በምታደርገው እንቅስቃሴ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ ምሁራን ከመቼውም ጊዜ በላይ በእውቀትና በሙያቸው ለመደገፍ ቃል እንደሚገቡ ተናግረዋል።
መንግሥት በግድቡ ድርድር ዙሪያ የወሰደውን አቋም ያደነቁት ምሁራኑ የተጀመረው ድርድር የኢትዮጵያን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲፈጸም በጋራና በግል ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉም በአቋም መግለጫቸው አመልክተዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ምርምር ተቋማት እንዲሁም ማህበረሰቡ ለግድቡ ስራ ፍጻሜ ባላቸው እውቀት ሙያና፣ ክህሎት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚቀጥሉና ሀብት በማፈላለጉ ስራም ከመቼውም ጊዜ በላይ ተግተው ለመስራት አቋም ይዘዋል።
የአባይ ወንዝ እውነተኛ ባለቤቶች ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ቢሆኑም እስካሁን ከባለቤትነት ጥቅሙ ያልተቋደሰውና በከባድ ድህነት ውስጥ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትሃዊ የጥቅም ተካፋይ ለማድረግ የግብጽና የሱዳን ወንድምና እህቶች የሰብአዊነት ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ነው ምሁራኑ የጠየቁት።
በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቅ ለሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል እንዲዘጋጁ ምሁራኑ በአቋም መግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል።