ቀጥታ፡

የመራጮች ምዝገባ ማስፈጸሚያ መመሪያ መዘጋጀቱን ቦርዱ አስታወቀ

መጋቢት 4/2012 (ኢዜአ) የመራጮች ምዝገባ ማስፈጸሚያ መመሪያ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ  አስታወቀ ።

የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ ለኢዜአ እንደገለጹት የመራጮች ምዝገባ፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚቋቋሙባቸው መንገዶችና በምርጫ ጣቢያዎች መከናወን የሚገባቸው ስራዎች በመመሪያው ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ከመኖሪያ ቄያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችና ሌሎች ከአካባቢያቸው ርቀው የሚገኙ ዜጎች የምርጫ ምዝገባና ለምርጫ በተለዩ  የምርጫ ጣቢያዎች (ስፔሻል ፖሊንጎች ) እንደሚስተናገዱ  ተናግረዋል።

ወይዘሪት ሶሊያና እንደተናገሩት ቀደም ሲል በነበሩት አገር አቀፍ ምርጫዎች የከፍተኛ  ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የምርጫ ምዝገባና  ምርጫ  በአንድ አካባቢ ይከናወን ነበር።

የዩኒቨርሲቲ  ተማሪዎች  የምርጫ ምዝገባና ድምጽ መስጫ ግን ቀደም ሲል ከነበሩት ምርጫዎች በተለየ መልኩ የሚከናወን መሆኑን ወይዘሪት ሶሊያና አብራርተዋል።

አማካሪዋ እንዳሉት  በመራጮች ምዝገባ  በሚካሄድበት  ወቅት ተማሪዎቹ በሚማሩባቸው  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ የሚገኙ ሲሆን በምርጫ ወቅት ደግሞ በመኖሪያቸው ወይም በሌላ አካባቢ ሊገኙ ይችላሉ ፤ ለዚህም ተማሪዎች የሚስተናገዱበት መንገድን በተመለከተ የምርጫ ቦርዱ ልዩ ውሳኔ በማስፈለጉ ውይይት እየተደረገበት ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ቦርዱ በነገው ዕለት  የምርጫ ክልሎች ካርታ  ይፋ እንደሚያደርግ ነው ወይዘሪት ሶሊያና የጠቆሙት።

ቀደም ሲል ከተካሄዱት ምርጫዎች  በተለየ መልኩ በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታና ሌሎች መረጃዎች የሚያሳይ ካርታ በጂ ኤይ ኤስ ታግዞ መዘጋጀቱንና ይህም መረጃ ይፋ እንደሚሆን አብራርተዋል።

በምርጫ ህጉ ላይ ያተኮረ ስልጠና ከፌዴራልና ክልሎች ለተውጣጡ ሶስት መቶ ለሚደርሱ ዳኞች  ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀን እንደሚሰጥ አክለዋል።

ስልጠናው ከምርጫ ጋር በተያያዘ በችሎትና በምርጫ ቦርድ መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች በመለየቱ ረገድ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑንም ወይዘሪ ሶልያና አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም