የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ጃፓናዊ ግለሰብ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ላይ ክትትል እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ጃፓናዊ ግለሰብ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ላይ ክትትል እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4/2012( ኢዜአ) በአዲስ አበባ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው ጃፓናዊ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው 25 ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ አንድ የ48 ዓመት ጃፓናዊ የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ግለሰቡ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ነበር ከቡርኪናፋሶ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት። ከአምስት ቀናት በኋላም ግለሰቡ ላይ የኮሮና ቫይረስ ምልክት በመታየቱ በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲገቡ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንዳሉት የተደረገው ምርመራ ውጤት የኮሮና ቫይረስ አሳይቷል።
ይሁንና የቫይረሱ ተጠቂ ጃፓናዊ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ከግለሰቡ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው 25 የሚጠጉ ሰዎችም ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳይሰራጭ ጠንካራ ክትትል እየተደረገ ይገኛል ሲሉም ነው ዶክተር ኤባ የተናገሩት።
ከመከላከል ስራዎች መካከል 30 በሚሆኑ የኢትዮጵያ የየብስ መተላለፊያዎች ላይ የልየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በሁሉም የአገሪቱ የድንበር አካባቢዎች የልየታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም እንዲሁ።
በክልሎችም የለይቶ ማቆያ ማዕከላት እንደተቋቋሙ አስታውቀዋል።
ቫይረሱ በተለይ ከ50 ዓመታት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ እንደሚበረታ የተገለጸ ሲሆን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ሁሉ እንደማይሞቱና የሞት ምጣኔው ዝቅተኛ እንደሆነ ዶክተር ኤባ አስረድተዋል።
ህብረተሰቡ ታማኝ ከሆኑ የመረጃ ምንጮች የሚወጡ መረጃዎችን ብቻ መከታተል እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።
መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ በማድረስ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።