ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ በአማራ ክልል 20 ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎች ሊካሄዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በመደገፍ በአማራ ክልል 20 ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎች ሊካሄዱ ነው
ባህር ዳር ሰኔ 22/2010 በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ዶክተር አብይ አህመድ የጀመሩትን የለውጥ ሂደት በመደገፍ በአማራ ክልል 20 ከተሞች ህዝባዊ ሰልፎች እንደሚካሄዱ የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለፁት ባህር ዳርና ደብረ ብረሃን ጨምሮ በ20 የዞንና የወረዳ ከተሞች ለሚካሄዱት የድጋፍ ሰልፎች በክልሉ መንግስት ህጋዊ እውቅና ተሰጥቷል። "በየከተሞቹ የሚካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቁ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል" ብለዋል። የድጋፍ ሰልፎቹ ዓላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ አንዣቦባት የነበረውን የመተሳሰብና የአንድነት ችግር" መደመር " በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዲታደስ በማስቻላቸው ህዝቡ ከጎናቸው መሆኑን ለማመላከት ነው። የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመሆን ሰልፉን ሰላማዊ ሆኖ በስኬት አንዲጠናቀቅ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታውቀው ህብረተሰቡም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል። "አብሮነትና ፍቅር የተራበው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ ክልሎች በደስታ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አገራዊ አንድነት እየደገፈ እንዳለው ሁሉ የአማራ ክልል ህዝብም በሰልፎቹ ሰላምና ፍቅርን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን ይዘምራሉ" ብለዋል። ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላስመዘገቧቸው ስኬቶች በክልሉ 13 ከተሞች የተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎች ያለ ፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቃቸውም ተመልክቷል፡፡