ቀጥታ፡

አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ያስከትላል...የምጣኔ ሀብት ባለሙያ

አዲስ አበባ መጋቢት 4/2012(ኢዜአ) አዲስ አበባ መጋቢት 04/2012 የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ ሳይተገበር ሃላፊነት በማይሰማቸው ነጋዴዎች  እየተደረገ ያለው የዋጋ ጭማሪ የሀገርቱን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ አስተያየታቸውን ለኢዜአ  የሰጡ የዘርፉ ባለሙያ  ገለጹ ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ዲፓርትመንት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር  ብርሃኑ  ደኑ  እንዳሉት  አዲስ የጸደቀው የኤክሳይዝ  ታክስ  ሳይተገበር ሃላፊነት  በማይሰማቸው  ነጋዴዎች  እየተደረገ ያለው  የዋጋ ጭማሪ  ኢንቨስትመንትን በማዳከምና ቁጠባን  በማመናምን የሀገሪቱን  ኢኮኖሚ ይጎዳል ብለዋል፡፡

የኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ በተወካዮች ምክር ቤት ቢፀድቅም ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከባለድርሻ

አካላት ጋር ተከታታይነት ያለው ውይይት ማድረግ አስፈላጊነቱን መሆኑንም ጠቅሰዋል ፡፡

የኤክሳይዝ ታክስም ሆነ ሌሎች ፖሊሲዎች  ሲቀረጹ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ያለው አንድምታ በደንብ መገምገም እንዳለበት ጨምረው ገልፀዋል፡፡

አገሪቷ በለውጥ ጉዞ ውስጥ እንደመሆኗ አሁን እየተደረጉ ያሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ይህን ታሳቢ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

የአዋጁ መውጣት የኢኮኖሚውን ሚዛናዊነት መጠበቁ፣ የሸማቹን ደህንነት ማረጋገጥ፣  አካባቢንና የሰዎችን ጤና  ለመጠበቅ በማስቻሉ  ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አግባብነት የሌለው የዋጋ ጭማሪ የሚደርጉ ተቋማት  ለጊዜያዊ ጥቅም   ደንበኞቻቸውን ሊያሳጣቸው  እንደሚችል ተገንዝበው  ከድርጊታቸው  እንዲቆጠቡ  መክረዋል፡፡   

ችግሩን ለመቅረፍም መንግስት የገበያ አማራጮች ከመፍጠር በተጓዳኝ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡   

የኤክስሳይዝ ታክስ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁን ተከትሎ ከየካቲት 6/2012 ጀምሮ  ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ነበር፡፡

አዋጁ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረግ በማስፈለጉ ተግባራዊ አለመደረ በማስታወስ  አሁን  በገበያ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ  በመሆኑ  ይህንን  ለመፍታት ከባለድርሻ

አካላት ጋር የጋራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሆነ የገቢዎች ሚኒስትር  ለጋዜጠኞች መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም