የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ከኅብረተሰቡ እና ከተለያዩ አካላት 15 ሚሊዮን ብር ሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ከኅብረተሰቡ እና ከተለያዩ አካላት 15 ሚሊዮን ብር ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4/2012(ኢዜአ) የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል 30ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር 15 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።
ከተሰበሰበው አጠቃላይ ገንዘብ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋው የተገኘው በአጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ መሆኑን የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኅሩይ ዓሊ ለኢትዮጵያ ዜና አገለግሎት ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ በዚህ መርሐ-ግብር በከፍተኛ ሁኔታ መሳተፉን አስታውቀዋል።
የማዕከሉ መዋቅራዊ አደረጃጀት ከማኅበረሰቡ ጋር በሚፈለገው ልክ በመድረስ እንዳንሰራ አድርጎናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለመዋቅራዊ አደረጃጀት ችግር ዋነኛ ምክንያት የገንዘብ እጥረት መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው በሚቆረጥ መዋጮ ማዕከሉን የመርዳት ፍላጎት ቢያሳዩም የማዕከሉ መዋቅራዊ አደረጃጀት ድጋፉን ለመሰብሰብ አዳጋች እንዳደረገው ገልጸዋል።
ችግሩን ለማስተካከል ማዕከሉ በቅርቡ የሕዝብ ግንኙነት እና ፕሮሞሽን ክፍል እንደሚያደራጅ አስታውቀዋል።
ክፍሉ ሲደራጅም በማኅበረሱ እና በማዕከሉ መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ ከዚህ የበለጡ ሥራዎች ለመስሥራት ይቻላል ብለዋል።
የንግድ ተቋማት፣ ፋብሪካዎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የሕፃናት የልብ ህሕሙማን መርጃ ማዕከል በ1981 ዓ.ም የተመሠረተ መንግሥታዊ ያልሆነና ለትርፍ ያልተቋቋመ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።
የልብ ሕክምና ማዕከሉ እስከ አሁን ለአራት ሺህ 800 የልብ ሕሙማን 70 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ነፃ የሕክምና አገልግሎት ሰጥቷል።
ማዕከሉ የልብ ታማሚ ሕፃናትን በመርዳት በከፍተኛ ደረጃ ሰብአዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ማዕከል እንደሆነ ይታወቃል።