በሀዋሳ ከተማ ተስተጓጉለው የነበሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል አንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ

76
ሀዋሳ ሰኔ 22/2010 በሀዋሳ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት የተቋረጡ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል እቅንቅሳሴ መጀመሩን የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ፡፡ የመንገድ ፣ የውሃ መፋሰሻ ቦዮችና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች እያከናወኑ  ካሉ ተቋራጮች ጋር ማዘጋጃ ቤቱ ተወያይቷል፡፡ የማዘጋጃ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ እንደገለጹት ግጭቱን ተከትሎ በከተማዋ በበጀት ዓመቱ የተጀመሩ የልማት ስራዎች  ባለፉት ሁለት ሳምንታት ተቋርጠው  ቆይተዋል፡፡ የተቋረጡት የልማት ስራዎች ማስቀጠል በሚቻልበት ላይ ግምገማ በማካሄድ አቅጣጫ  አስቀምጠው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በከተማው በበጀት ዓመቱ የአስፓልትና የድንጋይ ንጣፍ  መንገድ ፣ ወጪ ቆጣቢ ቤቶች ግንባታ፣ የፍሳሽ ውሃ ማስወገጃ ቦዮች ግንባታና ሌሎችም የተለያዩ ፕሮጀክቶች የማስቀጠል ስራ መጀመሩንም ወይዘሮ ይመኙሻል አስታውቀዋል፡፡ በውይይቱ የተሳተፉት የይርጋለም ኮንስትራክሽን ድርጅት ባልደረባ አቶ አበበ ለማ እንዳሉት በሀዋሳ ከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ድርጅቱ የሚያከናውናቸው የግንባታ ስራዎች ተስተጓጉለው ቆይተዋል፡፡ የይርጋለም ኮንስትራክሽን ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ወልደአማኑኤል በበኩላቸው "በሀዋሳ ብቻ ሳይሆን በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ውል ገብተን እየሰራናቸው ያሉ በርካታ የመሰረተ ልማት ተቋማት አሉን" ብለዋል፡፡ ከሳምንታት በፊት በሀዋሳ ከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ግንባታ  ማቋረጣቸውን ተከትሎ ስራ ያቆሙ ብዛት ያላቸው በጊዜያዊነት  የተቀጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚመለሱ ጠቁመዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም