ቀጥታ፡

ፓርቲዎቹ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ ነው

መጋቢት 3/2012 (ኢዜአ) በመጪው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለመሳተፍ የዝግጅት ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን የተለያዩ ፓርቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አገር አቀፍ እና የክልል ፓርቲዎች ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ዝርዝር ሁኔታዎችን የሚያስረዱ ሰነዶችና መስፈርቶቹን አሟልተው እስከ መጋቢት 03 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ እንዲያቀርቡና የምዝገባውን ስርአት እንዲጀምሩ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት ፓርቲዎች እንደተናገሩት፤ ምርጫ ቦርዱ በሰጠው ቀነ ገደብ መሰረት የደጋፊዎች ፊርማ አሰባስበው አስገብተዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ሀላፊ ወይዘሮ አልማዝ ሰይፉ እንደገለጹት፤ አገር አቀፍ እና የክልል ፓርቲዎች ማሟላት ያለባቸውን ግዴታ ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ መሰረት ፓርቲው እንዲያሟላ የሚጠበቅበትን የ10 ሺህ ደጋፊዎች ፊርማ አሰባስቧል።

በቀጣይም በቦርዱ መመሪያ መሰረት ለዕጩ ተወዳዳሪዎች የሚያስፈልገውን ከ3 ሺህ ያላነሱ ደጋፊዎችን ለማቅረብም በዕጩ ተወዳዳሪዎች በኩል ዝግጅት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲካሄድ የመንግስት አካላት ሀላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ቅንጅት ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ቡህ ሁሴን በበኩላቸው እንደ ክልል ፓርቲ ሟሟላት የሚጠበቅባቸውን የ4 ሺህ ደጋፊዎች ፊርማ አሰባስበው ለምርጫ ቦርድ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ የፓርቲያቸውን አባላት በየወረዳዎቹ የማወያየትና የማስተማር ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ ሉዓላዊነት ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ካሳዬ ዘገዬ በተመሳሳይ በምርጫ ቦርድ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ማሟላት የሚጠበቅባቸውን የአባላት ድጋፍ አሟልተው ለቦርዱ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም በቦርዱ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መከናወን ያለባቸውን ስራዎች ለማጠናቀቅ ፓርቲው ዝግጁ ነው ብለዋል።

ፓርቲው በቀጣዩ ምርጫ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ጫናዎችን ለመቋቋምና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግም አንስተዋል።

በምርጫ ቦርዱ ህግና መመሪያ መሰረት የፓርቲው አባላት ሰላምና ጸጥታን ከሚያደፈርሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ለማድረግ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም