ቀጥታ፡

የኩላሊት ህሙማን ቁጥር መጨመር በኢኮኖሚው ላይ ጫና እያሳደረ ነው - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2012 (ኢዜአ) የኩላሊት ህሙማን ታካሚዎች ቁጥር መጨመር በህብረተሰቡንና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ በመሆኑ ህብረተሰቡ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት የጤና ሚስቴር አሳሰበ።

የዓለም የኩላሊት ቀን "የኩላሊት ጤንነት ለሁሉም በሁሉም ቦታ" በሚል መሪ ቃል  በኢትዮጵያ የኩላሊት ህሙማን ማህበር አዘጋጅነት  ዛሬ ተከበሯል።

በዝግጅቱ ላይ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ነፃ የኩላሊት ምርመራ አድርገዋል።

በዚህም ህመሙን ቀድሞ በመከላከልና በበሽታው ከተያዙ በኋላ መደረግ ባለበት ጉዳይ በባለሙያዎች ትምህርት ተሰጥቷል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ሙሴ ገብረሚካኤል የኩላሊት በሽታ በቀላል ህክምና የማይድን  በመሆኑ ህብረተሰቡንና  መንግስትን  ለከፍተኛ  ወጪ  እየዳረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ጤና ሚኒስቴር ለበሽታው መንስኤ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመቀነስ  ከሚመለከታቸው  አካላት  ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

በርካታ የኩላሊት ህሙማን  በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና እያገኙ እንደሆነም  ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ህክምና የሚሰጡ ሆስፒታሎች ቁጥር በቂ አለመሆንና  የሚወጣው  ወጪ ከፍተኛነት ጠቅሰው  ህብረተሰቡ  ራሱን ከበሽታው  ለመከላከል  ቅድመ ጥንቃቄ  ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑት የደም ግፊት ፣ካንሰር፣ የስኳርና የኩላሊት ህመምተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን  ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የኩላሊት ህሙማን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ልሳነ ሰይፉ መንግስት የኩላሊት ህመምን ለመከላከልና በበሽታው ከተያዙ በኋላ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በሆስፒታሎች የጀመረው ስራ መልካም መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ከዚህ በላይ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ማህበሩ ህብረተሰቡ ነፃ የኩላሊት ምርመራና የምክር አገልግሎት  እንዲያገኙ  ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም