ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘችውን አቋም አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል--የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የያዘችውን አቋም አጠናክራ በመቀጠል ውሃውን በመጠቀም መብቷ ላይ ምንም አይነት ድርድር ማድረግ እንደማይጠበቅባት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አስታወቀ፡፡

አካዳሚው በጉዳዩ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉንተናዊ ሙያዊ ተሳትፎና አስተዋፅኦ ለማድረግ መዘጋጀቱንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዛሬ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ  "ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ የመጠቀም መብቷ በማንም ይሁንታና ክልከላ ላይ ያልተመሰረተ ሉዓላዊ መብቷ" መሆኑን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባትና ከ80 በመቶ  በላይ ህዝቦቿ በድህነት  አረንቋ ውስጥ  የሚገኙባት አገር መሆኑ እየታወቀ ለልማት የምታደርገው እንቅስቃሴ  በውጭ ሃይሎች  ጣልቃ ገብነት  ሊገታ  እንደማይገባ ነው መግለጫው ያተተው፡፡

መንግስት ዜጎቹን ከአስከፊ ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ የያዘው ወሳኙ አማራጭ የሰው ፣ የመሬትና የውሃ ሀብቱን በአግባቡ ማልማትና መጠቀም ነው።

ይህንኑ ለማሳካት የልማት ፖሊሲዎቹንና ዕቅዶቹን በመለየት ላለፉት ሁለት  አስርት ዓመታት  የተለያዩ የልማት  ስራዎች መተግበራቸው ይታወቃል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ዜጎችን ከአስከፊ ድህነትና ሰብአዊ ቀውስ በማውጣት ሀገራዊ የልማት ግቡ እውን እንዲሆን እንደሚያስችል በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፅጌ ገብረማርያም በዚሁ ጊዜ እንደጠቆሙት ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ  ማንንም በማይጎዳ ሁኔታ ተጠቅማ ለመልማት የምታደርገው ጥረት ሉአላዊ መብቷ ነው ብለዋል።

በድርድር ሂደቱ ከመነሻው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ታዛቢ ሆነው የገቡት  የአሜሪካ መንግስትና የአለም  ባንክ አካሄድ  ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ግድቡ በሌሎች አገራት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በተመለከተ አስቀድማ ጥናት በማድረግና በማረጋገጥ  ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ ግድቡን መገንባት መጀመሯን አውስተዋል፡፡

ይህን ያልተረዱ አካላት እና የግድቡ ግንባታ ጉዳት እንደማያስከትል በሚገባ የተረዳችው ግብፅ ሰላማዊ ሂደቱን ላለመቀበል የምታደርገውን እንቅስቃሴ በማቆም ወደ ድርድሩ መመለስ እንደሚኖርባትም አስገንዝበዋል፡፡

የአካዳሚው የቦርድ አባላት በውሃና በተለያዩ  ዘርፎች የሚሰሩ ምሁራንና ተመራማሪዎች  በተሳተፉበት በዚሁ  መግለጫ  ላይ ምሁራኑ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ በበኩላቸው እንደገለጹት "የአባይ ወንዝ ኢትዮጵያና ግብፅን ለዘመናት ያስተሳስር እንጂ የጋራ ሀብቱን በጋራ መጠቀም ሳይቻል" በርካታ ዘመናት አልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያሉባትን በርካታ ጫናዎች ተቋቁማ  ከራሷ ድንበር የሚመነጨው ውሃ የተፋሰሱ ሀገራትን በማይጎዳ 

መልኩ ለመጠቀም የጀመረችውን ሂደት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት ተገቢ አለመሆኑንና  ኢፍትሃዊ መሆኑን 

አብራርተዋል፡፡

የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ለአገራቸው ህዝብ የሚሰጡት የተሳሳተ መረጃ ህዝቡ ማወቅ ያለበትን እንዳያውቅ እያደረገው እንደሚገኝ የተናገሩት ምሁራኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ህዝቡን በማሳወቅ በኩል ጠንካራ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም