ቀጥታ፡

የለውጥ ጉዞው እንዲሳካ ሴቶች አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም ይጠበቅባቸዋል---አቶ ተመስገን ጥሩነህ

ባህር ዳር መጋቢት 3/2012 (ኢዜአ) ሴቶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤታማ የልማት ተግባራትን በማከናወን የለውጡን ጉዞ በማሳካት ታሪክ ሰሪ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

"የሴቶች መብትና ደህንነት መከበር ለሰላማችንና ለህልውናችን መሰረት ነው" በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል። 

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዓሉ ሲከበር እንዳሉት የኢትዮጵያ የኋላ አኩሪ ታሪኮች ሲፈተሹ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች በጦር ግንባር ጭምር ቀዳሚ ናቸው።

“የአሁኑ ትውድል ሴቶችም የቀደሙ ጀግና እናቶችን ታሪክ በመውረስ የዚህን ዘመን የሚመጥን የልማት ስራዎችን በማከናወን ታሪክ ሰሪ ሊሆኑ ይገባል”ብለዋል።

በክልሉ የሴቶችን አቅም በማጎልበት የለውጡ ዋና አራማጅ ሆነው እንዲዘልቁና የመሪነት ሚናቸውን እንዲወጡ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ በመሾም የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ እድሉ መሰጠቱንም አብራርተዋል። 

"ሴቶችን ወደ አመራርነት የምናመጣው ለማበረታታት ሳይሆነ እምቅ ችሎታቸውንና ታማኝነታቸውን በመጠቀም ወደ ብልፅግና የሚደረገውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ጭምር ነው" ብለዋል።

አሁንም ሴቶችን በእውቀት፣ በክህሎትና በአማለካከት በማብቃት ወደ ከፍተኛ የአመራርነት ደረጃ ለማምጣት እንደ ክልል በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አቶ ተመስገን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሴቶች እድል ከተሰጣቸው ካለባቸው የሴትነት ሃላፊነት በተጨማሪ ከወንዶች እኩልና ከዛም በላይ ታሪክ መስራት የሚችሉ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

“የሴቶችን ቀን ከማክበር ባለፈ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ናቸው።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማሳደግ የሴቶችን የቁጠባ ባህል ለማዳበርና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ጽፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ እመቤት ምትኩ በበኩላቸው “እንደ አማራ ክልል የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት አቅምና ተደራዳሪነትን ለማጎልበት ትምህርት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል”ብለዋል።

ያልተማረች ሴት በምታደርገው የህይወት ጉዞ ያሰበችውን ያክል ላይሳካላት እንደሚችል ገልጸው “ሴቶች በኢኮኖሚና በፖለቲካ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ቅድሚያ ትምህርት ላይ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ ሴቶች ፌዴሬሽን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር 400 ሴቶች የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እንዲማሩ እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ፌደሬሽኑ በልዩ ልዩ የአደረጃጀት ዘርፍ ከአንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ሴቶችን አቅፎ በተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲሳተፉ እያደረገ ይገኛል።

አለም አቀፍ የሴቶች ቀንንም አስመልክቶ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይም በየደረጃው የሚገኙ የሴት አመራሮች፣ የልዩ ልዩ ድርጅቶች ተወካዮችና የሴቶች አደረጃጀቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም