ቀጥታ፡

በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ መስራትን ልናጠናክር ይገባል.. የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አሶሳ መጋቢት 3/2012 (ኢዜአ) ከፖለቲካ ልዩነቶችና አስተሳሰቦች ባለፈ በጋራ ሀገራዊ ጉዳይ የተጀመረውን ተቀራርቦ የመወያየትና የመመካከር ልምድ እንደሚያጠናክሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

አመራሮቹ በርዕዮተ-ዓለምና በፖለቲካዊ ልዩነቶች ምክንያት የተፈጠረውን መራራቅ ትተው በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መጀመራቸውን ተናግረዋል። 

ደስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሺየቲቭ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በአሶሳ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንዳሉት ቀደም ሲል የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ብቻ በጠላትነት ይተያዩ ነበር።

“በሃገራችን ጉዳይ የሃሳብ ነጻነትን ተከትሎ የመነጋገር ልምድ መዳበር አለበት” የሚሉት ሃላፊው “ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጉዳዩ ተገቢ እና አስፈላጊ እንደሆነ እያመንን መጥተናል” ብለዋል፡፡

“የፖለቲካ ልዩነታችንን ወደጎን ትተን ህዝብን በሚጠቅሙ እና በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ መነጋገር ችለናል” ሲሉም ተናግረዋል። 

በአንዳንድ የፖለቲካ አመራሮች መካከል በሃገራዊ ጉዳዮች ልዩነት እያጣን ነው ያሉት ሃላፊው ለዚህ መስተካከል የፖለቲካ አመራሮች ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የሚያደርጉት ጥረት ወሳኝ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

“አሁን የተገኘው ውጤት አብረን ከመመገብ ጀምሮ በችግሮቻን ላይ በግልጽነት እና በመቀራረብ መወያየታች ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“የእርስ በርስ መቀራረብ እና መደማመጥ በአባሎቻችን እና በህብረተሰቡ ውስጥ ሠላም እንዲፈጠር ያስችላል” በማለት አቶ ቀጄላ አብራርተዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ወይዘሮ ሶፊያ አልማሙን በበኩላቸው በፖለቲካ አመራሮች መካከል የሚታየው ልዩነት በጋራ ጉዳዮች ላይ በውይይት የሚፈታና የሚያስተሳስር ነው።

አንዳንዶቹም በሚያራምዱት የፖለቲካ ልዩነት ብቻ በጠመንጃ ሁሉ የሚፈላለጉ እንደነበሩ ገልጸው የውይይት መድረኮችን በየጊዜው መፍጠርና ማሳተፍ መሰል ችግሮችን ከማስቀረቱም ባለፈ መተማመንንም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ቢኖሩም በሰከነ መንገድ በመነጋገር ለሃገራዊ ለውጡ የሚጠቅም ስራዎችን ለማከናወን መደማመጥና መግባባት እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊና ለፍትህ/ኢዜማ አመራር አቶ ግርማ ሠይፉ “በፓርቲ አመራሮች መካከል አንዱ ሌላውን የኢትዮጵያ ጠላት አድርጎ ከማየት ተላቀው በመነጋገር ሃገራችንን እንዴት እናስቀጥል የሚል ልምድ እየዳበረ መጥቷል” ይላሉ፡፡

በፖለቲካ አመራሮች ግንኙነት የማይመቹ ነገሮች ሲያጋጥሙ ጉዳዩን ከባለቤቱ ጠይቆ ከመረዳት በተጨማሪ እውነት ሆኖ እንኳን ቢገኝ በውይይት የማስተካከል አስፈላጊነት ላይም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም በውይይት መድረኮች በጋራ ተቀምጠን በመግባባት መለያየታችን በተከታዮቻችን ዘንድ በበጎ የሚወሰድ በመሆኑ ለሃገር ሠላም ፋይዳው የጎላ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም