ቀጥታ፡

ለኢትዮጰያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ የሚውል 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ቃል ተገባ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3/2012(ኢዜአ) ማልታ ጊነስ ለኢትዮጰያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ የሚውል የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ቃል ገባ። "መልካምነትን እንጋራ" በሚል በጀመረው እንቅስቃሴ ድጋፉን እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ድርጅቱ ድጋፉን ለማድረግ የወሰነው የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል የበርካታ ህጻናትን ህይወት በመታደግ ላይ እንደሚገኝ በመረዳታቸው መሆኑን የተቋሙ የብራንድ ሃላፊ ወይዘሪት የአብስራ ጌታቸው ተናግረዋል።

የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ሰባት ሺህ የሚጠጉ ህክምና ጠባቂዎች ቢኖሩትም በአቅም ውስንነት በአመት 500 የልብ ታካሚዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በገንዘብና በህክምና ግብአቶች እጥረት መስራት ከምንችልበት አቅም አንድ ሶስተኛውን ብቻ እየተጠቀምን ነው በማለት የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ህሩይ አሊ ተናግረዋል።

በዚሁ የአሰራር ፍጥነት ከቀጠልን ህክምናውን ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ያሉትን ታካሚዎች ለማስተናገድ 14 አመት ይፈጅብናል በማለት የችግሩን አሳሳቢነት አሳይተዋል።

ሌሎች ድርጅቶች ተመሳሳይ ድጋፍ ቢያደርጉልን የተጠባባቂ ታካሚዎቹን ህክምና ማግኛ ጊዜ ከሶስት እስከ አራት አመት ማሳጠር እንችላለን ብለዋል።  

በማልታ ጊነስ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የ"መልካምነትን እንጋራ" ፕሮጀክት አካል በሆነው የባለፈው ዓመት የበጎ አድራጎት ዘመቻ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉ ይታወሳል።

ከተቋቋመ ሶስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማዕከል እስከ አሁን 70 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ለአራት ሺህ 800 የልብ ህሙማን የነፃ ህክምና አገልግሎት መስጠቱ በመግለጫው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም