ቀጥታ፡

ለህዳሴ ግድብ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን...አርቲስቶች

መጋቢት 3/2012(ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማንኛውንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የተለያዩ አርቲስቶች ተናገሩ።

አርቲስቶቹ የግድቡን ወቅታዊ ሁኔታና የሥራ እንቅስቃሴ በቦታው ሄደው የተመለከቱ ሲሆን፤ ግንባታው ለኢትዮጵያውያን የጥንካሬ ምስክር ነው ብለዋል።

ስለ ግድቡ የሚነገረውና በቦታው ያለው እውነታ ፍጹም የተለያየ መሆኑን ያስረዱት አርቲስቶቹ፤ ሥራው  ያለማቋረጥና በፍጥነት እየተሠራ መሆኑን ማየታቸውን ገልፀዋል።

በተለይ በግንባታው ላይ በቀጥታ የተሠማሩት ሠራተኞች በበረሃው ያለው ሙቀት ሳይበግራቸው 24 ሠዓታት  በሥራ ላይ መቆየታቸው ያላቸውን የአገር ፍቅር በግልጽ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ክረምት በሁለት የሃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሃይል ለማመንጨት እያደረገችው  ያለው ጥረት  መቀጠል እንዳለበትም አርቲስቶቹ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሰጥተዋል።

ተዋናይት መታሰቢያ ታደሰ በሰጠችው አስተያየት "ግድቡ 24 ሰአት ቆመው በመሠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች  በደንብ እየተሠራ እንደሆነ ስታይ በየቀኑ ግድቡን የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሃላፊነት ወስደው እንደሚንቀሳቀሱ ስታያቸው እኔ ምንም ቃል የለኝም፤ ከጠበኩት በላይ እጅግ በጣም መግለፅ የማልችለው ነው። ትላለች።

አርቲስት ፋሲል ግርማ በበኩሉ "በ2013 ሁለቱ ሃይል ማመንጫ ከተሠራ ትልቅ ነገር ነው። ስለዚህ ሥራውን  አይቻለሁ ምስክር ነኝ በጣም ደስ ብሎኛል"።

ኢትዮጵያዊያን ከአሁን በፊት ለገጠሙን ማናቸውም ችግሮች አንድ ሆነን እንደተሻገርነው ሁሉ የህዳሴውን ግድብ  እውን ለማድረግም አብረን መሆን አለብን ሲሉም አርቲስቶቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ለህዳሴው ግድብ ግንባታ በሙያ፣ በገንዘብና በእውቀት ከሚደረጉ ድጋፎች በተጨማሪ ለህዳሴው ግድብ የሚጠየቅ ምንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አርቲስት ማክዳ አፈወርቅ  "ሁል ጊዜ ትልቅ ነገር ስገነባ ፈተና ይገጥማል፣ ከባድ ነገሮች ይመጣሉ፣  ግን  የየተነሳህበት አላማ ስለሚበልጥ አላማው ላይ  መቆዬት እንዳለብንና እስከመጨረሻው  ግብ እስከሚደርስ  ድረስ እሱ ላይ መታገል እንዳለብን አምናለሁ፤  እና ሁላችንም በጋራ የጀመርነውን  ነገር በተለያዩ  ፈተናዎች  እጅ ከመስጠት አንድ ላይ በጋራ ሆነን ማየት የፈለግነውን ተስፋ በጋራ ማየት አለብን ብዬ አምናለሁ" ነው ያለችው ።

አርቲስት ፋሲል ግርማ በበኩሉ "ስለ ኢትዮጵያ ህልውና አስቦ ህዝቡን ማስተማር ነው፣  የኛ ሥራ  በየጊዜው ወደዚህ ሥፍራ  እየመጣን፣ እየተከታተልን ምን ደረጃ ላይ  ደረሰ እያልን  እየሠራን ለወገኖቻችን  ግድቡ እንደዚህ ደርሷል፣ እንደዚህ ተሠርቷል ብለን የምንሠራበት ጊዜ ነው፤  ስለዚህ ይሄ የሁላችንም  ትብብር  የሚጠይቅ ነው " በማለት ያስረዳል።

ግድቡ ግንባታው ከተጀመረ በዚህ በያዝነው የመጋቢት ወር ዘጠነኛ ዓመት የሚሞላው ታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ 

ሃይል ማመንጫ ግድብ  አጠቃላይ የግንባታው ሂደት 71 በመቶ ደርሷል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም