ቀጥታ፡

የጥላቻ ንግግርን ማገድ የመናገር ነጻነትን መንፈግ አይደለም

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2012( ኢዜአ) የጥላቻ ንግግርን ማገድ የመናገር ነጻነትን መንፈግ አይደለም ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በየሁለት ወሩ ለምትዘጋጀው ነጋሪ መፅሄት ሙያዊ ትንታኔ የሰጡ ምሁራን እንደገለጹት "በቅርቡ በህግ ተርጓሚው ምክር ቤት የፀደቀው የጥላቻ ንግግር አዋጅ ያልተገቡ ሀሳቦችን ስርዓት ለማስያዝ እንጂ የመናገር ነጻነትን ለመንፈግ የወጣ አይደለም፡፡ "

''በሩ ገርበብ ይበል!'' በሚል ርዕስ በተስተናገደው ሐተታ ላይ ምሁራኑ እንደገለጹት አዋጁ "የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ የመረጃ ስርጭትን አገሪቱ ባሏት ህጎች መፍታት ባለመቻሉ የወጣ ተጨማሪ ህግ ነው።"

በኢትዮጵያ ህገ-መንንግስት አንቀጽ 29 የማሰብ ነጻነትና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ስር በግልጽ እንደተደነገገው "ማንኛውም ሰው በንግግርም ሆነ በጽሁፍ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ሃሳቡን የመግለጽና የማንጸባረቅ መብቱ ያልተገደበ "ነው፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀጽ 6 ላይ የወጣቶችን ደህንነት ፣ የሰውን ክብርና መልካም ስም ለመጠበቅ ፣ እንዲሁም ጦርነት ቅስቀሳዎችንና ሰብአዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎች ለመከላከል ሲባል እነዚህ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣል እንደሚችል  ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ላሉ ብሄርን ከብሄር ፤ ኃይማኖትን ከኃይማኖት ሊያጋጩ የሚችሉ ሀሳቦችን ለመቆጣጠር ያለው ጠቀሜታ ቀላል አለመሆኑንም ነው ምሁራኑ ያብራሩት፡፡

አዋጁ መብትን እንዳይገድብና የዴሞክራሲ ስርዓቱን እንዳያቀጭጭ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተግባራዊ መደረግ እንዳለበትም ምሁራኑ ያሳስባሉ፡፡

የጥላቻ ንግግር ሲባል ድምጽን ፣ጹሁፍን ፣ ምስልን ፣ቅርጻ ቅርጽን ፣የድምጽና ምስል ቅንብሮችንና ፣ ካርቶኖችን ያካተተ መሆኑን የህግ ምሁሩ ዶክተር ውብሸት ሙላት ይጠቅሳሉ፡፡

ምሁሩ “መጥላት ላለብን የጥላቻ ንግግር የተጨማሪ ህግ አስፈላጊነት” በሚል ርእስ መጽሄቷ ላይ ባሰፈሩት ሐተታ እንደጠቆሙት “ማንኛውም የዘር ጥላቻን፣ የሌላ አገር ዜጋን ወይም ስደተኛ በጭፍኑ መጥላት ፣ትዕግስት አልባና አግላይ የሆነ ብሄርተኝነትን፣ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ብሄረሰቦችን ሰበብ እየፈለጉ መገለል እንዲደርስባቸው የሚሰብኩ፣ የሚያሰራጩ የሚያነሳሱ፣ የሚያበረታቱና ትክክል እንደሆኑ ለማስረዳት የሚደረጉ ጥረቶች የያዙ ቃላዊ ገለፃዎች ፣ጹሁፎች ፣ ምስሎችና ሥዕሎች ፣ ቅርፃ ቅርጾች መጠቀም ነው” እንደሆነ ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያ ህዝብን፤ ከህዝብ ብሄርን ከብሄር የሚያጋጩ የጥላቻ ንግግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸውን የተናገሩት ደግሞ በጠቅላይ አቃቤ ህግ ስር የመገናኛ ብዙሃንን ህግ ለማሻሻል የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጎሹ ናቸው።

 ሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት ባወጣቻቸው ህጎች ውስጥ ስለመረጃ ነፃነትና ስለንግግር ነጻነት ያልጠቀሰችበት ቦታ እንደሌለ በመጠቆም አፈጻጸሙ ላይ ችግር እንደነበረበት ሰብሳቢው  ጠቅሰዋል፡፡

በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድም የጉዳዩ አሳሳቢነት በስፋት እየተነገረ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ዋናው የጥላቻ ንግግር መገለጫ" በንግግር በሌሎች ላይ እርምጃ ማስወሰድ ፣ ቡድኖችን ለእኩይ ድርጊት ማነሳሳት እንዲሁም አመፅ መቀስቀስ ላይ ያነጣጠረ" ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ 

በአገሪቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጥላቻ ንግግሮች ሳቢያ በማህበረሰቡ ውስጥ ፍራቻና የእርስ በርስ መጠራጠሮች ነግሰዋልም ነው ያሉት።  

ይህም ሊሆን የቻለው ዜጎች በማንነታቸው፣ በሃይማኖታቸውና በቋንቋቸው ምክንያት ለተለየ አደጋ በመጋለጣቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ለተከሰቱ ሰብዓዊ ጉዳቶች ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የተላለፉ የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በፀረ ሽብር ህጉ አተገባበር ላይ የተንጸባረቀውን "መሰረታዊ የመናገር ነጻነት መገደብ እንዳይከሰት" ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ማሳሰባቸውንም የኢዜአ የየካቲት ወር ነጋሪ መጽሄት ዘግባለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም