የአጼ ፋሲል ቤተ መንግሥት የአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የአጼ ፋሲል ቤተ መንግሥት የአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆነ
ጎንደር ኢዜአ 03/2012 በአማራ ክልል ቅርሶችን የምሽት ገጽታ የሚያሳይ በኤሌትሪክ ብርሃን ቴክኖሎጂን ለማስተዋወቅ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡
የአየርላንድ መንግሥት የልኡካን ቡድን ያዘጋጀው የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግሥትን የምሽት ገጽታን የሚያሳይ የአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ የሙከራ ፕሮግራም ትናንት ማምሻውን ተካሂዷል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ መላኩ አላምረው በሙከራ ፕሮግራሙ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ ቴክኖሎጂው በአለም አቀፍ ደረጃ የክልሉን ሰው ሰራሽ ቅርሶች በማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ ያግዛል፡፡
ያደጉ ሀገራት የአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ በመተግበር ቅርሶቻቸውን የምሽት ገጽታ በአማራጭ የማስተዋወቂያ ዘዴ በስፋት የሚጠቀሙበት አሠራር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በቴክኖሎጂውም የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግሥትና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪ የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትን ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት በሚታይበት በጥምቀት ክብረ በዓል ላይ ቴክኖሎጂውን በስፋት ለማስተዋወቅ መታቀዱን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በገና በዓል የምሽት ገጽታውን በአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አንጂነር በሪሁን ካሳሁን በበኩላቸው፤ ጎንደር በኪነ-ሕንፃ ግንባታ ቀደምት አሻራ ካላቸው የሀገራችን ከተሞች ቀዳሚ ስፍራ እንዳላት ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ቀደምት የኪነ-ጥበብ አሻራዎች ከተማዋን ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ጠቁመዋል፡፡
የአየርላንድን ብሄራዊ ቀን ምክንያት በማድረግ የልኡካን ቡድኑ የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትን የምሽት ገጽታ በአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ ያደረገው ጥረት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ትስስር የሚያጠናክር እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአየርላንድ ጉዳዮች ተጠሪ ሚስተር ፓትሪክ ማክማነስ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት "ይህንን ማራኪ ገጽታ ያለውን የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስት በአካል ተገኝቼ በምሽት ብርሃን በማየቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል"፡፡
የአየርላንድ ዓለም አቀፍ የአረንጓዴ ብርሃን ኢንሼቲቭ ፕሮጀክት የአየርላንድን ቅርሶች በዓለም ደረጃ በማስተዋወቅ ቱሪስቶች በብዛት ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡምቹ ሁኔታ ሲፈጥር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ኢንሼቲቩ ባለፈው አመት የላሊበላን አለም አቀፍ ቅርስ የምሽት ገጽታ በአረንጓዴ ብርሃን ቴክኖሎጂ የማስተዋወቅ ስራ መስራቱንም አስታውሰዋል፡፡
የብርሃን ቴክኖሎጂውን ለማስተዋወቅ በአጼ ፋሲል ቤተ-መንግሰት ውስጥ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራል፣ የክልልና የጎንደር ከተማ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የከተማው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡