የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከአጋር ባንኮች ጋር በቅርበት መስራቱ የክፍያ ስርአቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍ እንደሚረዳው አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከአጋር ባንኮች ጋር በቅርበት መስራቱ የክፍያ ስርአቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍ እንደሚረዳው አስታወቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2010 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከባንኮች ጋር በቅርበት መስራቱ የክፍያ ስርአቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍ እንደሚረዳው አስታወቀ። ምርት ገበያው ዛሬ ከአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በክፍያ ፈጻሚነት የአገልግሎት አሰጣጥ ስምምነት ተፈራርሟል። ስምምነቱም ተገበያዮች ግብይቱን በፈጸሙ ማግስት ለአቅራቢዎች የሸጡበትን ገንዘብ በቀጥታ ከገዢው የባንክ ሂሳብ ወደ ሂሳባቸው እንዲዞር ለማድረግ የሚረዳና አጠቃላይ የግብይት ሂደቱን ለማዘመን እንደሚያግዝም ተገልጿል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘው ነገራ በስምምነቱ ወቅት እንደ ተናገሩት፤ የክፍያ ስርአቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍና ለማዘመን ከባንኮች ጋር በቅርበት መስራታችን ወደፊት አስተማማኝ የግብይት የክፍያ ስርአት እንዲኖር ያስችላል። ምርት ገበያው ከዚህ በፊት ከ13 ባንኮች ጋር ተፈራርሞ ከ11 ባንኮች ጋር እየሰራ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለት ባንኮችም ወደ ክፍያ ስርዓቱ እየገቡ መሆኑ ተገልጿል። አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክም 14ኛ አጋር ሆኖ የክፍያ ስርዓቱ ውስጥ ለመካተት ዛሬ ስምምነት ተፈራርሟል። ከባንኮቹ ጋር መስራት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በባንኮቹ አማካይነት በአጠቃላይ ለምርት ግብይት ገቢ የተደረገው ገንዘብ መጠን 182ነጥብ8 ቢሊዮን ብር ሲሆን ለሻጭ ደግሞ ወጪ ተደርጎ የተከፈለው 177ነጥብ2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ስራ አስፈጻሚው አስታውሰዋል። የአዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይሉ ዓለሙ በበኩላቸው "14ኛው አጋር ባንክ ሆነን ከምርት ገበያው ጋር ለመስራት ተፈራርመናል፤ ይህ ደግሞ ባንኩንም፣ ላኪውንና አቅራቢውን የሚጠቅም ስምምነት ነው'' ብለዋል። ክፍያ መፈጸም የሚቻለው አባል በሆኑት ባንኮች በኩል ብቻ በመሆኑ የባንኩ ደንበኛ የሆኑ ላኪዎች ክፍያ ለመፈጸም ይቸገሩ እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ከምርት ገበያ ድርጅቱ ጋር የተደረገው ስምምነት የባንኩን ደንበኞች የክፍያ ችግር የሚፈታ መሆኑን ገልጸዋል። ምርት ገበያ ድርጅቱ በቀጣይነት አገልግሎቱን በተሻለ ሁኔታ ለመፈጸም የክፍያ አፈጻጸም ስርዓትን በባንኮች በኩል እንዲሆን ለማስቻል እንደሚሰራ ተገልጿል። ምርት ገበያው በበጀት ዓመቱ በ11 ወራት ጊዜ ውስጥ 31 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ስድስት መቶ ሰላሳ ቶን የግብርና ምርቶች ማገበያየት መቻሉን አስታውቋል።