ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን ለ43 የፈጠራ ባለቤቶች እውቅናና የምስክር ወረቀት ተሰጠ

ነገሌ (ኢዜአ ) መጋቢት 2/2012፡- በኦሮሚያ ጉጂ ዞን በፈጠራ ስራ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ላበረከቱ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተማሪዎችና መምህራን ዛሬ በነገሌ ከተማ እውቅናና የምስክር ወረቀት ተሰጠ፡፡
አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን በማቅረብ ልማትን ለመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ እውቅና ያገኙ ተማሪዎችና መምህራን ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ከኑ ቦሩ በፈጠራ ስራ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎቹን ላበረከቱት 43 ተማሪዎችና መምህራን እውቅናና የምስክር ወረቀቱን ሰጥተዋል፡፡

እውቅና ለማግኘት ከቀረቡት መካከል በዋናነት የሰብል ማምረቻ የማርና የአይብ ማቀነባበሪያ፣ የልብስ ማጠቢያ ከጸሀይ ፣ ውሀና ጨው የኤሌክትርክ ኃይል በማመንጨት የሚያመርቱ የፈጠራ ስራዎች ይገኙበታል፡፡

የፈጠራ ስራዎቹ በውጭ ከተመረቱ ተመሳሳይ ቴክኖሎጂዎች ከ20 እስከ 150 ሺህ ብር የሚደርስ የዋጋ ልዩነትና ቅናሽ እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡

ምክትል አስተዳደሪው  እንዳሉት መንግስት በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ለፈጠራ ስራዎችና ባለቤቶቹ ልዩ ድጋፍና ትኩረት ይሰጣል፡፡

በቀጣይም በጉጂ ዞን የፈጠራ ስራ ባለቤቶችን ለማበረታታት የሚሰጠው ድጋፍና እውቅና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

ከተሸላሚ መምህራን መካከል መምህራን መካከል የቦሬ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መምህር ታገል መስፍን ባቀረቡት የማርና የአይብ ማቀነባበሪያ የፈጠራ ውጤት ያገኙት እውቅናና የምስክር ወረቀቱ ለበለጠ ስራ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል፡፡

"ባለኝ እውቀት ከዚህ የተሻለ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን በማዘመን ለሀገሬ እድገት የድርሻየን እወጣለሁ" ብለዋል፡፡

የነገሌ ከተማ ነዋሪና የአስረኛ ክፍል ተማሪ ዮናታን ማቲዎስ በበኩሉ ባለፈው ዓመት ያቀረበው የመንጃ ፈቃድ መለማመጃ ሶፍት ዌር ያስገኘለት እውቅና ዘንድሮም የተሻለ ይዞ ለመቅረብ እንደረዳው ገልጿል፡፡

የጸሀይ ኃይል በመሰብሰብ በማታ ወጭ የማይጠይቅ ብርሀን የሚሰጥ የፈጠራ ስራ በማቅረቡ በድጋሚ እውቅና ማግኘቱ አስደስቶታል፡፡

"ባለን እውቀትና ክህሎት ሁላችንም የአቅማችንን ከልብ ከሰራን ሀገራችንን ከድህነትና ኋላቀርነት የማናወጣበት ምክንያት አይኖርም" ብሏል፡፡

ከትምህርቱ በተጓዳኝ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ የፈጠራ ስራ በማቅረብ ታዋቂነትን ለማትረፍ እንደሚጥር  ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም