በበርበሬ ምርት ላይ ዋጋ የጨመሩ ነጋዴዎች ድርጅታቸው ታሸገ - ኢዜአ አማርኛ
በበርበሬ ምርት ላይ ዋጋ የጨመሩ ነጋዴዎች ድርጅታቸው ታሸገ
ሰቆጣ (ኢዜአ ) መጋቢት 02/2012 ፡- በሰቆጣ ከተማ አስተዳደር አለአግባብ በበርበሬ ምርት ላይ የተጋነነ ዋጋ የጨመሩ ነጋዴዎች ድርጅታቸው አንዲታሸግ መደረጉን የከተማው ንግድና ገበያ ልማት ጽህፋት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መላሽ ወርቃለማው ለኢዜአ እንደተናገሩት የታሸጉት ድርጅቶች በከተማው የበርበሬ ጀምላ አከፋፋይ የሆኑ 11 ነጋዴዎች ናቸው።
ነጋዴዎቹ ምንም ዓይነት የበርበሬ ምርት እጥረትም ሆነ የዋጋ ጭማሬ ሳይኖር እንዳለ አድርገው በማስወራት አለአስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ አድርገው ተገኝተዋል።
ጭማሪውም አንድ ኪሎ ግራም 80 ብር ይሸጥ የነበረን በርበሬ ወደ 120 ብር ከፍ በማድረግ ነው።
በዚህም በርበሬን አላግባብ በሆነ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ አከፋፋይ ነጋዴዎችን ግብር ኃይል ተቋቁሞ የካቲት 30/2012 ዓ.ም. ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ መጋዝኖቻቸው እንዲታሸጉ መደረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል።
ከነጋዴዎቹ ጋር ዛሬ በተደረገው ውይይትም ምርቱን ቀደም ሲል ሲሸጡበት በነበረው ዋጋ እና ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ለሸማቹ እንዲያቀርቡ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
በሸቀጦች ዋጋ ላይ በየጊዜው አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ቸርቻሪ እና ጅምላ አከፋፋዮች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ህብረተሰቡ አለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ሲጋጥመው ሊጠቁም እንደሚገባ አሳስበዋል።