ቀጥታ፡

ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ገለፁ

አዲስ አበባ  መጋቢት 2/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሲያደርጉት የቆዩትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ገለፁ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድቡን ስትገነባ በዚህ ወንዝ ልማትን የማከናወን ተፈጥሯዊ መብቷን በመጠቀም መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር እና አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ማየት የሁሉም ዜጋ ፍላጎት በመሆኑ ለግንባታው መጠናቀቅ ሲያደርጉት የነበረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በታሪክ አጋጣሚ ለትውልድ በሚሸጋገር የልማት ሥራና ለእድገት የጎላ አስተዋዕኦ በሚኖረው የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ድጋፋቸውን በማድረግ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በሥራቸው ያሉ አደረጃጀቶችን በመጠቀም ሲያደርጉት የቆየውን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንጉዳይ እሸቴ በበኩላቸው በስራቸው ባሉ 14 ማህበራት እና 265 ቅርንጫፎች ከዚህ ቀደም ለግድቡ ግንባታ ሲያደርጉት የቆየውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ግድቡ በተለይም ከድህነት አረንቋ ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝና በዚህም ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በየትኛውም መልኩ የግድቡን ግንባታ ከዳር ለማድረስ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ብዙ ሥራዎች ቢሰሩም በግድቡ ዙሪያ ግን እምብዛም የተሰሩ ሥራዎች አለመኖራቸውንና ይህ ሁኔታ አሁን መቀየር እንዳለበት አርቲስት ቢኒያም ወርቁ ተናግሯል።

በዚህም መንግስት ለኪነጥበብ ዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በግድቡ ዙሪያ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች እንዲሰሩ ማድረግ እንዳለበት ጠቁሟል።

ለዚህም እሱን ጨምሮ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግሯል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው ሕብረተሰቡ  ለታላቁ ህዳሴ  ግድብ ግንባታ  የተለያዩ  ድጋፎችን  ሲያደርግ  መቆየቱን አስታውሰዋል።

የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት 9ኛ ዓመት ዘንድሮ ሲከበር ህብረተሰቡን የሚያሳትፉ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።

አሁን የሚታየውን የህብረተሰቡ መነሳሳትና ቁጭት በመጠቀም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ወይዘሮ ሮማን ገልጸው፣ በዚህም በዘንድሮው በጀት አመት በተደረገ እንቅስቃሴ እስካሁን ከ397 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አሁን በተጀመረው እንቅስቃሴ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ሥራዎች ለመስራት እንቅስቃሴ እንደሚደረግ ወይዘሮ ሮማን ተናግረዋል።

በገቢ ማሰባሰብ ሥራው ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰበ ዕቅድ እንዳለም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም